AMN – ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ባለፉት ዓመታት የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋትና የንግድ አሠራርን በማስተካከል ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ እንዳሉት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በንግዱ ዘርፍ የተመቸና ዘመናዊ የንግድ ሥርዓትን እውን ለማድረግ፣ የምርት አቅርቦትን የማሻሻልና ገበያን የማረጋጋት ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም መሰረት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዜሮ ማዕከላት ተነስተው የገበያ ማዕከላት ቁጥር ዛሬ ላይ 7 መድረሱን፣ እንዲሁም የሰንበት ገበያዎች ቁጥርም ከዜሮ ወደ 264 መድረሳቸውን ወ/ሮ ሀቢባ አስታውቀዋል።

መዲናዋ በ2019 በጀት ዓመት እና በቀጣይ አምስት ዓመታት ትኩረት ካደረገችባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የንግድ ስርዓቱን ከከተማዋ እድገት ጋር ማዘመን አንዱ መሆኑን ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ተናግረዋል።
በንግዱ መስክ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ ለመከላከል የዲጂታል ቁጥጥር ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ፣ ለገበያ መረጋጋት የድርሻቸውን የሚያበረክቱ ተጨማሪ የግብይት ማዕከላትን መገንባት የቢሮው ቀጣይ ውጥኖች ናቸው።
በዚህም መሰረት የሰንበት ገበያዎችን ቁጥር አሁን ካለበት 264 ወደ 357 ለማድረስና ነዋሪዎች ባሉበት አካባቢዎች፣ እንዲያውም ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ቦታዎች ጭምር ተደራሽ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 4 የግብይት ማዕከላትን በመገንባት የቁጥር አድማሱን ከፍ ለማድረግ የታለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የንግድ ተቋማት በተቆጣጣሪዎች በኩል ከሚነሱ የሙስና ስጋቶች፣ በዘፈቀደ የመዝጋትና የመክፈት ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በቴክኖሎጂ ለማስቀረት ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ የሆነ አዲስ ስርዓት ለህብረተሰቡ ይዞ ለመምጣት ቢሮው ተግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ አስታውቀዋል።
በወርቅነህ አቢዮ
See less