የከተማችንን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እጅግ ጠቃሚ እና ገንቢ ተግባቦትና ዝግጁነት ፈጥረናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የከተማችንን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እጅግ ጠቃሚ እና ገንቢ ተግባቦትና ዝግጁነት ፈጥረናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የከተማ አስተዳደሩ የቀጣይ አምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድና የ2019 በጀት ዓመት ዝርዝር እቅድ ውይይት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በውይይታችን እቅዶቹን ይበልጥ ተጨባጭ በማድረግ በቀጣይ አምስት ዓመታትም አልቀን በመፈፀም፣ የከተማችን ነዋሪ የጣለብንን እምነት እና የሰጠንን ሀላፊነት ሳንሸራርፍ ለመፈፀም፣ የከተማችንን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እጅግ ጠቃሚ እና ገንቢ ተግባቦት እና ዝግጁነት ፈጥረናል ብለዋል።

ከሀገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂያችን በመነሳት ህዝባችንም በድጋሚ ሲመርጠን “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌታዊ ሀገር” ብለን የገባነውን ቃል ለመፈፀም እንደ አዲስ አበባ “አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት” ለማድረግ የጀመርነውን ጉዞ ዋና ርዕያችን አድርገናል ሲሉም ገልጸዋል።

ለእቅዳችን ስኬት መሰረቶች የሆኑት ባለፋት አምስት ዓመታት አቅደን አልቀን ያስመዘገብነው ውጤት፣ የህዝብና መንግሥት ከደህነት የመውጣት ፍላጎት፣ በከተማችን የተፈጠረው የስራ ትጋት፣ በታማኝነት ማገልገል፣ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በፍጥነትና በጥራት የመፈፀም ልምድ፣ በጀትን በመቆጠብ መጠቀም ትልቅ ስንቅ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይ ትኩረታችንም ተቋማዊ ብቃትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ የዘመነ ቴክኖሎጂ በሚጠቀም የላቀ አገልግሎት መስጠት፣ የተቀናጀ ጥራት ያለው ሰፊ መሰረት ልማት በፍጥነት መገንባት፣ አዲስ መሰረተ ልማት መገንባት ብቻ ሳይሆን ነባሮቹን በሚገባ ማስተዳደር፣ የንፁህ መጠጥ ውኃና የቤት አቅርቦት ማሳደግ፣ የማህበራዊ ዘርፍ (ጤና፣ ትምህርት…) ተደራሽነትና ጥራት እንዲሁም ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ አልቀን መፈፀም፣ ዓለማቀፍ ስታንዳርድ ያሟላ የጤና አገልግሎት መስጠት ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም የጤና ቱሪዝም ማዕከል መሆን፣ የከተማችንን የቱሪዝም መዳረሻ ከተማነት ማረጋገጥ፣ አዲስ አበባን ህፃናትን ለማሳደግ ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ ማድረግ፣ ለወጣቶች ተጠቃሚነት፣ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲሁም በኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ባህል በማድረግ ማህበራዊ ፍትህን ማንገስ፣ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማትን ማጠናከር፣ እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህን ማንገስ፣ አምራችነትን ማሳደግ፣ ተረጂነትን መቀነስ፣ የስራ እድልን በሰፊው መፍጠር፣ የከተማ ግብርና፣ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ማዘመን፣ ፅዳትና የቆሻሻ አወጋገድን ባህል ማድረግ … ወዘተ፤ በአጠቃላይ ከተማችንን ጽዱ፣ ውብ እና ለሁሉም የምትመች ከተማ ማድረግ የእቅዳችን ትኩረቶች ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው ፣ የእቅዳችን ቅኝትም ስትራቴጂክ እይታ ያለው፤ ራዕያችንን ለማሳካት አቅዶ መተግበር፤ የተለጠጠ፣ አካታች፣ ፍትሃዊ እንዲሁም አሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል።

ይህ የእቅድ ውይይት አመራራችን በዋናነት እቅዱን በተሟላ ሁኔታ የተረዳ፣ ስትራቴጂክ አመራር የሚሰጥ፣ በአስተሳሰብ አንድነት የሚቆም፣ ከተለያየ የጥቅም ትስስር ነፃ የሆነ፣ የይቻላል መንፈስን የተላበሰ፣ በአፈፃፀም ተቀራራቢ የሆነ፣ ትጋት እና የአመራር ዲሲፒሊን ያለው፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት እያሰፈንን ህዝቡ የከተማችንን ራዕይና ግብ የተጋራ እንዲሆን በተለየ መንገድ የሄድንበት የውይይት መድረክ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ልማትን በመንግስት ብቻ ማሳካት እይቻልም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪዎች፣ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ፣ የግሉን ዘርፍ ማበረታታት፣ በጊዜ የለንም መንፈስ 24/7 የመፈጸም ባህላችንን ይበልጥ አሳድገን በከተማችን ለማሳካት የተወጠነውን ትልቅ ራዕይ ለመፈፀም በላቀ እንተጋለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review