ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቀጨኔ-አምባሳደር-ጊዮን-ኢሬቻ-ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መረቁ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቀጨኔ-አምባሳደር-ጊዮን-ኢሬቻ-ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መረቁ

AMN – ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ፣ የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል ብለዋል፡፡

ይህ የ351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና የ10 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለውን የኮሪደር ልማት ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ሁሉንም አካታች የሆነች አዲስ አበባን የመገንባት ራዕያችንን እውን የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት መንገዶችን እና የተቀናጁ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ያካተተ በመሆኑ፣ ይህ ልማት ይበልጥ ተደራሽ እና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ የከተማ ከባቢን ይፈጥራል ብለዋል።

የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እንዲሁም የውሃ ትርዒት ማሳያዎች ለመዝናኛና ማህበራዊ ግንኙነት አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚያበረክቱ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና ከ100 በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ መሙላት የሚያስችሉ ስምንት የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላት የዘመናዊ መሠረተ ልማቱን አቅም ይበልጥ ያጠናክራሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ በወንዝ አስተዳደር፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ስፍራዎች አማካኝነት የአካባቢ ጥበቃን ከከተማ ገፅታ ለውጥ ጋር እያቀናጀን እንገኛለን ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ይህ ልዩ የኮሪደር ልማት አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን መፍጠር ያስቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የተዘጋጀው የገበያ ማዕከል ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው አካባቢ ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የዕደ ጥበብ ምርቶችን እንዲያመርቱ፣ ለማሳያና ለመሸጫ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ሲሆን፣ የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከ ደግሞ የግብርና አምራቾችን ከገበያው ጋር ያገናኛል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመልዕክታቸው የእኛ ርዕይ ለዛሬውና ለሚቀጥሉት ትውልዶች ውብ ብቻ ሳትሆን ምርታማና ሁሉንም አካታች እንዲሁም ህዝቧን የምትመጥን ከተማ መገንባት ነው! ሲሉ ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review