AMN – ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ተግዳሮቶች ተፈትኖ ያለፈ የድል ሠራዊት መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ተናገሩ፡፡
119ኛው የሠራዊት ቀን እየተከበረ ይገኛል።
በአከባበሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ኢትዮጵያ በፅናትና ጀግንነት የታነፀ ሰራዊት ባለቤት ናት ብለዋል፡፡
የሀገር ሉዐላዊነትን እና የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች፤ ሠራዊቱ አስተማማኝ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የድል ሠራዊትነቱን የሚያስቀጥሉና በምድር፣ በአየር እና በሳይበር ቴክኖሎጂዎች ላይ ከፊት የሚያሰልፈው ስራ መሰራቱንም ገልፀዋል።

የሀገርን ዳር ድንበር ሉዓላዊነት እና የህዝብን ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር፣ ለቀጣናው እና ለመላው አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ በሚያስችል መልኩ ስትራቴጂካዊ ዝግጁነቱን ያረጋገጠ ሠራዊት መሆኑንም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ ከየትኛውም ወገን የፖለቲካ ፍላጎት ገለልተኛ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፤ ይልቁንም የሀገር ሉዓላዊነትንና የህዝብን ሠላም ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሰራዊት መሆኑን ተናግረዋል።
በበላይሁን ፍስሃ