AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ 33ኛ ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ “ብሩህ ነገን በዛሬ አዕምሮአችን” በሚል መሪ ቃል እያካሄደ ይገኛል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በመዲናዋ የትምህርት ጥራትን፣ ተደራሽነትንና ፍትሃዊነትን ለማረጋገት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
እስካሁን በዘርፉ የተደረገው ኢንቨስትመንት ፍሬ ማፍራቱን በተማሪዎች ውጤት መሻሻል እያረጋገጥን ነውም ብለዋል።
በተሰሩ ስራዎች ውጤታማነት እየተሻሻለ መምጣቱን የተናገሩት ከንቲባዋ፣ ይህም በ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል የማለፊያ ነጥብ ውጤት ላይ እየታየ ነው ብለዋል።
በተለይ በ6ኛ እና በ8ኛ ክፍል ከአመት አመት እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ ውጤት የስራ ውጤት መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፣ በትምህርቱ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት የተማሪዎችን የማለፍ ምጣኔ ከፍ የማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በስነ ምግባር፣ በእውቀት፣ በክሎትና በፈጠራ የበለፀገ ትውልድን ማፍራትን ያለመ ነው ብለዋል።
በአምስት ዓመት እቅድ ውስጥ የማሳለፍ መጠን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ችግር ፈቺ ትውልድ በመፍጠር የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ትውልድ የሚቀረፀው ከታች መሆኑን በመረዳት ከቀዳማይ ልጅነት ጀምሮ ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ያደረገ ስራ በመንደፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በዚህም መሰረቱ ላይ ጥሩ ዘር በመዝራት ችግር ፈቺ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንና ለውጦች መመዝገባቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ፣ የተገኘውን ውጤት ለማላቅ መምህራን በእልህ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የትምህርት ጉባኤውም የመጡ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ድክመቶችን ነቅሶ አውጥቶ ለማረም በርካታ አስተዋጽኦ እንዳለው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
በራሄል አበበ