AMN- መስከረም 2/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ 2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በልደታ ክፍለ ከተማ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 500 ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር አካሄደ።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር፤ መተባበር እና መረዳዳት የኢትዮጵያውያን የቆየ ባህል መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም፤ መርሐ ግብሩ በበዓል አቅመ ደካማ ወገኖች እንዳይቸገሩ የጸጥታ መዋቅሩንና ባለሃብቶችን በማስተባበር የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ድጋፉ ኢኮኖሚያዊ ችግር የገጠማቸው ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማድረግ እና “አለንላችሁ፤ ከጎናችሁ ነን” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ መዘጋጀቱንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ምክትል ስራ አስፈጻሚ እና የስራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አዳሙ በዛብህ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ዓመት መግቢያ በክፍለ ከተማው በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ ከ32 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የማዕድ ማጋራት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ለ500 ወገኖች ለእያንዳንዳቸው 5 ሊትር ዘይት እና 25 ኪሎ ግራም ዱቄት መበርከቱንም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የበዓል መዋያ አስቦ ይህንን መርሃ ግብር ማዘጋጀቱ ትልቅ የአዲስ ዓመት ስጦታ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ናቸው።
የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚዎች ለኤ ኤም ኤን በሰጡት አስተያየት፤ የተደረገላቸው ድጋፍ በቤታቸው ውስጥ የነበረውን ክፍተት እንደሸፈነላቸው በመጠቆም ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በትዝታ መንግስቱ