ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና የሚጫወት ነው- የምክክሩ ተሳታፊ የሐይማኖት አባቶች

AMN- ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም

ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ የተሻለ ፖሊሲ ለመቅረፅ በግብዓትነት የሚያገለግል እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን የምክክሩ ተሳታፊ የሐይማኖት አባቶች ገለጹ።

ሐምሌ 8 የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደቀጠለ ነው፡፡

የምክክሩ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች፤ ምክክር በሃይማኖት መጻሕፍት የተጻፈ የሰው ልጆች ከራሳቸውና ከሌሎች ጋር የሚታረቁበት ቁልፍ መሣሪያ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።

አፈ ዕምር አባ ገ/ሥላሴ ጌትነት፤ ምክክር ያለፉ ችግሮችን በውይይት መፍታትና በቀጣይ ለሀገሪቱ የተሻለ ፖሊሲ ለመቅረፅ በግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑን አብራርተዋል።

ሀገሪቱ ችግሮቿን በምክክር ለመፍታት መወሰኗ በራሱ የችግሩ መፍትሔ መጀመሩን እንደሚያሳይ የገለጹት አፈ ዕምር አባ ገ/ሥላሴ ጌትነት፤የምክክር ሂደቱ “ከእኔ” ወጥተን ወደ “እኛ” እንድንመጣና በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።

ሃጂ ኢብራሂም በሪሶ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ መታማመንና መግባባት በማምጣት ሀገሪቱ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የሰላም ምሳሌ እንድትሆን የሚያስችል ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ እያንዳንዱ ዜጋ ሀሳቡን በነጻነት የሚያስረዳበት እና ሀሳቦች የሚከበሩበት አሳታፊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review