ከእሳት አደጋ ስጋት ወደ ተስፋ ብርሃን፡ የገብስ ሜዳ ነዋሪዎች አዲስ ምዕራፍ

AMN – መስከረም 03/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6፣ በጎነት መንደር በተለምዶ «ገብስ ሜዳ» እየተባለ በሚጠራው ሰፈር የሚኖሩ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በከፋ የኑሮ ውጣ ውረድና በጠባብ ቤቶች ውስጥ በመኖራቸው ለተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ተጋልጠው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ከተማ አስተዳደሩ ባስገነባላቸው አዲስ እና ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች አዲሱን ዓመት በድምቀት በማክበራቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።

አዲሱን ዓመት በአዲሱ መኖሪያቸውና ከአዲስ ተስፋ ጋር የተቀበሉት ነዋሪዎች፤ ያንን ፈታኝ ጊዜ ተሻግረው በዘመናዊ የመኖሪያ አፓርታማዎች ውስጥ በሰላም፣ በድምቀት እና በደስታ የሚኖሩበትን አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን በምስጋና አንስተዋል።

የመኖሪያ ቤት እድል ተጠቃሚው አቶ ታምራት ታደሰ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሲናገሩት በዓል ሲከበር ሰው ሁሉ ደስታውን ብቻ ያደምቃል፤ እኛ ግን በአንድ በኩል በዓል አክብረን በሌላ በኩል እሳት የቱ ጋር ይነሳል ይሆን? በሚል ፍርሃትና በስጋት እንጠብቅ ነበር» በማለት ያሳለፉትን አስጨናቂ ጊዜ ያስታውሳሉ።

የቤቶች ጥበት በመኖሩ ምክንያት እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ ፈታኝ እንደነበር፣ እንዲሁም የሰፈሩ ጠባብነትና የንጽህና እጦት ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ጭምር አጨልሞት እንደነበር ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።

ሌላኛዋ የቤቱ ተጠቃሚ ወ/ሮ ወጋየሁ ወርቁ በበኩላቸው፣ የቤተሰብ ብዛትና የቤት ጥበት የፈጠረውን ጫና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ ላይ ግን ክብራቸውን የሚመጥን አኗኗር መጀመራቸውን በደስታ ተናግረዋል።

የቀድሞው ጠባብ፣ ጽዳት የጎደለው እና የእሳት አደጋ ሰለባ የነበረው አካባቢ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ገልጸው፤ መንግስት ላደረገላቸው የመኖሪያ ቤት እድል ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዛሬ ላይ ልጆቻችን ሳሎን አንጥፈው በሰላም ይተኛሉ፤ እኛም በንጹህ መኝታ ቤት እናርፋለን ያሉት ወ/ሮ ጸሃይ ዋቆ የተባሉ ነዋሪ፣ የተሰማቸው ደስታ ከልክ በላይ በመሆኑ ከደስታ ብዛት ማልቀሳቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ማህበራዊ አገልግሎቶች ድረስ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍ ያነሱት ወ/ሮ ወጋየሁ፥ ልጆቻችን በሰርቪስ እየተማሩ፣ ቁርሳቸውንና ምሳቸውን እየበሉ በኩራት እያደጉ ነው ሲሉ የአዲሱን ህይወት ስኬት መስክረዋል።

የገብስ ሜዳ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን አስቸጋሪና መራራ የኑሮ ታሪክ ዛሬ ላይ በአዲስ ተስፋ እና በምቹ አፓርታማዎች ተክተውታል።

የሰፈሩ መለወጥ የብዙዎችን እንባ ያበሰ፣ የበርካታ እናቶችንና አባቶችን ሰቆቃ ያቃለለ እና ህይወታቸውን በዘላቂነት የቀየረ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review