AMN-መስከረም 9/2019 ዓ.ም
“የሚጨሰው ጠረጴዛ” የተሰኘ በፕሮፌሰር በቀለ መኮነን የተዘጋጀና ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ለመቀራመት በርሊን ላይ የመከሩበትን ሂደት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያሳይ ቋሚ አውደ ርዕይ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከፈተ፡፡
የአውደ ርዕዩ አዘጋጅ ፕሮፌሰር በቀለ መኮነን እንደገለጹት፤ አውደ ርዕዩ አፍሪካዊያን ለነፃነት የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ በአንፃሩ ቅኝ ገዦች የአፍሪካን አንጡራ ሀብት ለመቀራመት የሄዱበትን ርቀት በውል የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲሁም የትናንትን ታሪክ በአግባቡ የሚዘክር ለነገ ትውልድም ትምህርትን የሚለግስ ነው፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል መሰል ታሪኮች በአግባቡ የሚዘከሩበት እና ትውልድ ከትናንት ተምሮ በቀጣይ ጠንካራ አብሮነትን የሚገነባበት ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት በውል የሚገልጥ የኢትዮጵያዊያንን አይበገሬነት የሚያንጸባርክ ብሎም የጥቁር ህዝቦች ምልክተ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዘመናዊ አሰራሩን በማላቅ የጎብኝዎች የስበት ማዕከል ለመሆን በቅቷል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሀገር ታሪክ ወደ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ እና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
በተመስገን ይመር