የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የህልውና፣ የሉዓላዊነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው

AMN – መስከረም 10/2019 ዓ.ም

ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ፣ የባህር በር ባለቤት ባለመሆኗ የንግድ እንቅስቃሴዋ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል።

እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ቁጥር እና የውጭ ንግድ ፍላጎትም የባህር በር ባለቤት መሆንን ለሀገሪቱ የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ አድርጎታል።

ቀጥተኛ የባህር በር ማግኘት በውጭ ወደቦች ላይ የሚወጣውን እጅግ ውድ የወደብ እና የትራንስፖርት ወጪ በእጅጉ ይቀንሰዋል።

በተጨማሪም የንግድ ሂደቶችን በማፋጠን፣ የትራንስፖርት ጊዜን በማሳጠር እና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ከፍ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የራሷ የባህር ላይ ንግድ እና የጸጥታ መዋቅር መኖሩም ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ደህንነት አስተማማኝ ዋስትናን ይሰጣል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚደግፈው እና የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላም የሚያረጋግጥ ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን ለአህጉሪቱ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት አሳይተውት የነበረውን አርአያነት ያለው ቁርጠኝነት በመድገም፣ የባህር በር ጥያቄን ተገቢነትና ፍትሃዊነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ የማስተባበር ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋት እና ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ አንጻር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በዘላቂነት ሊፈታ የሚገባው የሁሉም ወገኖች ትብብር የሚጠይቅ አብይ ብሔራዊ ጉዳይ ነው።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review