አዲስ አበባ የስፖርት ቱሪዝም እና የዘመናዊ ልማት ማሳያ

AMN – መስከረም 10/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የኮሪደር ልማቶች እና የከተማ ማሻሻያ ሥራዎች አማካኝነት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን በብቃት የምታስተናግድ ውብ ከተማ ሆናለች።

ይህ ሁለገብ ዕድገት ለከተማዋ ኢኮኖሚ እና መሠረተ ልማት ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

የከተማ አስተዳደሩ ያከናወናቸው ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ከተማዋን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች በብቃት ዝግጁ አድርገዋታል።

ለዚህም ማሳያው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች፣ የጂምናዚየም ማዕከላት፣ የልምምድ ሜዳዎች እና የኦሎምፒክ መንደሮች ተገንብተውና ታድሰው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ነው።

ከተማዋን ከዋና ዋና የስፖርት ማዕከላት ጋር የሚያገናኙ ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲሁም ዘመናዊ ሆቴሎች ለተወዳዳሪዎችና እንግዶች ምቾትን ፈጥረዋል።

ይህ ሁለገብ ዕድገት በግንባታ፣ በሆቴል አስተዳደር፣ በቱሪዝም እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያስቻለ ሲሆን፣ ከተማዋም እውነተኛ የስፖርት ቱሪዝም መዳረሻ በመሆን የውጭ ምንዛሪ ግኝቷን ማሳደግ ችላለች።

በመዲናዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን እያገኘ የመጣው ሚክስድ ማርሻል አርት ውድድር፤ የዚህ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ማሳያ ሆኗል።

ከተማዋ ከሚክስድ ማርሻል አርት ውድድሮች በተጨማሪ በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን በብቃት ማስተናገድ ጀምራለች።

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ውድድሮች በመዲናዋ መካሄዳቸው የወጣቶችን ክህሎት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።

በመዲናዋ በየጊዜው የሚካሄዱ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ከማድረጋቸው ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ዘላቂ መሠረተ ልማት እየተሟላላት መሆኑን ያመላክታሉ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review