ለመጭዎቹ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡- የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን

AMN- መስከረም 10/2019 ዓ.ም

ለመጭዎቹ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሀብተየስ ዲሮ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማረጋጋትና መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች በየአቅራቢቸው ማግኘት እንዲያስችሉ በእሁድ ገበያዎች በኩል ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በዚህም ከክልሎች ጋር በመነጋገር አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች በስፋት ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ በመደረጉ በአዲሱ አመት በከተማዋ በሚገኙ የእሁድ ገበያዎችና የግብይት ስፍራዎች ላይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል፡፡

ባሳለፍነው አዲሱ አመትም 1 ቢሊየን ብር የሚሆን የምርት ግብይት መፈፀሙን ነው አቶ ሀብተየስ የጠቀሱት፡፡

በከተማዋ በ290 ሸማች ማህበራት ስጋ ቤቶች ላይ የሉካንዳና የቅርጫ በሬዎችን በማቅረብ አዲሱ አመት ግብይቱ ስኬታማ ሆኖ አልፏል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ ለመጭዎቹ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ የባህል አልባሳት ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ዝግጅት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በቀጣይ ለሚከበሩት በዓላት ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በሚገኙ መገበያያ ስፍራዎች የምርት እጥረት እንዳይከሰት ቅኝት እያደረገ መሆኑን አቶ ሀብተየስ አስታውቀዋል፡፡

በደሴ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review