AMN- መስከረም 11/2019 ዓ.ም

በአፍሪካ ውስጥ ብቸኛው የራሷ ፊደል ያላት፣ ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ ቡናን ለዓለም የሰጠች፣ ልዩ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ናት፡፡
ከአንድ ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያላት ይህች ታላቅ ሀገር በህዝብ ብዛት በዓለም 10ኛ በአፍሪካ ደግሞ 2ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን ታሪካዊ ክብር ጠብቃ ከመኖር ባለፈ፣ ለሌሎችም መጠለያ በመሆን ከሶሪያ፣ ከኤርትራ፣ ከየመን፣ ከኢራቅ፣ ከቡሩንዲ እና ከሌሎች ሀገራት ተሰደው የመጡ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን አስጠልላለች።

በተጨማሪም ከ400 ሺህ በላይ ኤርትራውያን በሰላም የሚኖሩባትም የበርካቶች አስተማማኝ ቤት ናት፡፡
ይህችን ገናና እና ጥንታዊት ሀገር በወግ እና በስርዓት ገንብቶ ለትውልድ ማሸጋገር ግን የትናንት ታሪክን ከመዘከር በላይ የዛሬን ራዕይና ጠንካራ ስራ ይፈልጋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውብ፣ ጥንታዊት እና ታላቅ ሀገር ናት፡፡
ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ ፍላጎትና በጊዜያዊ ጉዳዮች ሳይወሰኑ፣ ከ10 እስከ 15 ዓመታት አርቀው በማየት እና በማሰብ በትብብር ሊገነቧት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያን በስርዓት መገንባት ከቻልን፣ ለእኛ ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አፍሪካውያንም አርአያ የሚሆን እና የሚተርፍ ታላቅ ሀገራዊ አቅም መፍጠር እንችላለንም ነው ያሉት፡፡

ለዚህም በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በወታደራዊ ዘርፎች ለትውልድ የሚሻገር አስተማማኝ መሰረት የመጣል ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የዚህ አርቆ አሳቢነት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በ10 እና በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ስመ-ጥር ሀገር እንድትሆን ማድረግ እና ለመቶ ዓመታት የሚዘልቅ የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው፡፡
በማንኛውም ታላቅ የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እንቅፋቶችና ፈተናዎች ማጋጠማቸው አይቀሬ ነው።
በመደመር እሳቤ የተጀመረው የዕድገት ጉዞ ሊያደናቅፉ የሚሞክሩ ሀይሎች ቢኖሩም፤ እንቅፋቶችን በአንድነት እና በትብብር ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ይገለጻል፡፡
በሀገሪቱ እየተተገበሩ ባሉ አጠቃላይ የሪፎርም ስራዎች ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል። ኢትዮጵያ ድንቅ፣ ታሪካዊ እና የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን በንግግር ሳይሆን በተግባር ተገልጾ ለዓለም እየታየ ያለበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ጥንታዊቷና ውቧ ሀገር ኢትዮጵያ የነበረችበት ታሪካዊ ማማ እና አሁን ያለችበት አቅም የሚመጥናት የወደፊት ተስፋ አላት፡፡
በእምነት እና በተስፈኝነት ከተሰማራን፣ አሁን ካለንበት ፈተና ሁሉ አልፈን እኛ እና አባቶቻችን ከነበርንባት ኢትዮጵያ የተሻለች፣ ያማረች እና የበለጸገች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንችላለን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግና ላይ ያለቸውን ተስፋ አጋርተዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ