AMN – መስከረም 13/2019 ዓ.ም
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአየር ኃይሏ ላይ ባደረገችው ግዙፍ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ ፣ የአየር ክልል ጸጥታዋን አስተማማኝ መሠረት ላይ ማስቀመጥ ችላለች።
የዘመናዊ ራዳር መሣሪያዎችን እና የድሮን ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማቀናጀት ረገድ አየር ኃይሉ የደረሰበት ደረጃ ፣ ሀገሪቱ ራሷን በሙሉ አቅም ሉዓላዊነቷን እንድትጠብቅ አስችሏታል።
የዚህ ዘመናዊ የጦር አቅም መጎልበት ኢትዮጵያን ለመበታተን እና የጥፋት አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ሌት ተቀን ለሚታትሩት ጠላቶች እና የውስጥ ተላላኪ ባንዳ ኃይሎች ከባድ መርዶ ሆኖባቸዋል።
የኢትዮጵያን ሰላም ማየት የማይፈልጉ እና ሀገሪቱን ሁልጊዜም በውጥረት ውስጥ ለማቆየት የሚመኙ አካላት የሚሞክሯቸው ትንኮሳዎች በአየር ኃይሉ ቅጽበታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየተቀለበሱ ይገኛል።
የድሮን ቴክኖሎጂን ከሌሎች የሰራዊቱ ክፍሎች ጋር በማቀናጀት የተከናወኑ የደህንነት ሥራዎች የጠላቶችን የትንኮሳ አቅም ሙሉ በሙሉ ያመከኑ ናቸው።
ፈተናዎችን በድል በመወጣት ፣ ካለፉት ክስተቶች ትምህርት በመውሰድ እና ከፍተኛ የሪፎርም ስራ በመስራት ተቋማዊ እድገትን ያስመዘገበው አየር ኃይሉ፣ የትኛውንም የጠላት ትንኮሳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል።

ሀገርና ሕዝብን ከጠላት እኩይ ተግባር ለመጠበቅ ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን ጭምር የሚሰጡ አብራሪዎች እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ያሉት ይህ ተቋም፣ የኢትዮጵያ የማይበገሩ ንስር ኃይሎች ማዕከል ነው።
የጠላቶች የዘወትር ሕልም የኢትዮጵያን መዳከም ማየት ቢሆንም፣ አየር ኃይሉ የገነባው ጠንካራ አቅም ግን ይህን የጠላት ከንቱ ምኞት መና አስቀርቷል። ሠራዊቱ በፈጠረው የላቀ የብቃት ዝግጁነት የጠላቶች ሴራዎች በሙሉ እየከሸፉ ይገኛሉ፡፡
ለዜጎች እና ለወዳጅ ሀገራት የአየር ኃይላችን ጥንካሬ ልብን የሚያሞቅ ታላቅ የሀገር ኩራት ሲሆን፣ ሕዝቡም በሰራዊቱ ላይ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አቅም በዘመናዊ መንገድ መገንባቱ የሰላማችን እና የልማታችን ዋስትና ሆኖ ቀጥሏል።
በወርቅነህ አቢዮ