AMN- መስከረም 14/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ኅብረ-ብሔራዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ብዝሃነቷን የውበትና የጥንካሬ ምንጭ በማድረግ ለነገው ሀገራዊ ከፍታ የሚሆን የወል ትርክት እየገነባች ትገኛለች።
ኅብረ ብሔራዊነት የዚህች ሀገር የውበት መገለጫና የብዝሃነቷ ማኅተም ነው።
የተለያዩ ባህሎች፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችና ማንነቶች በአንድ ላይ ተጋምደው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ፤ አንድነቷን የምታጸናው በዚሁ ውብ ብዝሃነቷ ነው።
የወል ትርክት ደግሞ እነዚህን የተዋቡ ብዝሃነቶች አቀናጅቶ ጠንካራና የማይበጠስ ብሔራዊ ትስስር የሚፈጥር ድልድይ ነው።
ይህንን የጽኑ አንድነት ማማ ከፍ ለማድረግ እንደ አድዋ ድል ያሉ መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ የተጋፈጧቸውንና በአሸናፊነት ያጠናቀቋቸውን ታላላቅ የታሪክ አጋጣሚዎች እንደ ሀገራዊ ኩራትና የአንድነት ማገር መጠቀም ይገባል።
ልዩነትን የሚያሰፉ አፍራሽ ትረካዎችን በምክንያታዊና በሳይንሳዊ የታሪክ ጥናቶች መተካት የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
ለዚህ ስኬት ደግሞ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ የጋራ እሴትን፣ መቻቻልንና አብሮነትን የሚያስተምሩ ይዘቶችን ማካተት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
በተለይም ሚዲያዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጥላቻን ከማሰራጨት ይልቅ የብዝሃነት ውበትን እና የወል ትርክትን የሚያጎሉ ይዘቶች ላይ በማተኮር ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንደገለጹት፤ ከታሪክ ቁርሾ ወጥቶ ሀገረ-መንግሥትን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም የወል ትርክት መገንባት ወሳኝ ጉዳይ ነው።
የወል ትርክት ልዩነቶችን በአንድ ሀገራዊ ግብ ሥር በማሰባሰብ ብዝሃነትን የጥንካሬ ምንጭ የማድረግ ዓላማ ያለው ትልቅ ሐሳብ መሆኑን መግለፃቸውም የሚታወስ ነው።
በበረከት ጌታቸው