AMN – መስከረም 15/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ዉሃን ጨምሮ ያላትን የተለያዩ የተፈጥሮ ጸጋዎችንና የሰዉ ሃይሏን ተጠቅማ የመበልጸግ ምቹ ዕድል ቢኖራትም እስከ ዛሬ ድረስ ግን ይህንን ህልሟን ማሳካት አልቻለችም፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ህልሟን እዉን እንዳታደርግ እንቅፋት ከሆኑ በርካታ ምክንያቶች መካከል የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በሃገሪቱ ላይ የሚፈጽሙት ጫናና ተጽእኖ ቀዳሚዉ መሆኑን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
እነዚህ የሃገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች የኢትዮጵያን እድገት፤ ልማት እና ሰላም የማይሹ በመሆናቸዉ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዉ የኢትዮጵያን የመበልጸግና የማደግ ዉጥን ሲያደናቅፉ ኖረዋል፡፡
ታሪካዊ ጠላቶቹ፤ የዉስጥ ባንዳዎችን ቀጥረዉ የሃገሪቱን ሰላምና ልማት ከማደፍረስ፤ ወንድማማች ህዝቦችን በብሄርና በሃይማኖት አጀንዳዎች እርስ በርስ እንዲጋጬ ከማድረግና መሰረተ ልማቶቿን ከማዉደም ጀምሮ በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዳይኖር የተለያዩ ሴራዎችን ሲፈጽሙ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያመላክታሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ስትጠቀምበት የነበረዉን የባህር በር ያጣችዉ የዉስጥ ባንዳዎች ከዉጭ ሃይሎች ጋር በፈጠሩት ጥምረት ሲሆን በዚሁ ምክንያት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ለመቆየት ተገዳለች፡፡
ሃገሪቱ አባይን ጨምሮ የትላልቅ ወንዞች፤ ሃይቆች፤ ማዕድናት፤ ለም አፈር፤ የእንስሳት ሃብትና የሌሎችም ጸጋዎች ባለቤት ብትሆንም በእነዚህ ሃብቶቿ እንዳትጠቀምና ብልጽግናዋን እንዳታረጋግጥ በርካታ ተጽእኖዎችን ሲያደርሱ ኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅማ እንዳታደግ ከተደረጉባት በርካታ ጫናዎችና ተጽእኖዎች መካከል የአባይ ወንዝና የታላቁ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ሲሆን ሃገሪቱ በተፈጥሮ ባገኘችዉ ጸጋ ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ተገዳለች፡፡

በተለይ ግብጽ የአባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመጠቀም ካላት ስግብግብ ፍላጎት የተነሳ እንደ ሻዕቢያ፤ ህገወጡ የህወሃት ቡድን እና ጽምዶን በመጠቀም የሃገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ከማደፍረስ አልፋ በዲፕሎማሲዉ ዘርፍም በርካታ ጫናዎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡
የለዉጡ መንግስት ከመላዉ የሃገሪቱ ዜጎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ጫናዎችና ሴራዎች ምክንያት ግንባታዉ ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ የቀረዉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በጽናት በማጠናቀቅ ብርሃን እንዲያመነጭና ቀጣናዉንም በሃይል እንዲያስተሳስር አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚያደርሱትን የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁሞ የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ እዉን ለማድረግ በመስራት ላይ የሚገኘዉ የለዉጡ መንግስት ከቅርብ አመታት ወዲህ በእነዚሁ ታሪካዊ ጠላቶች ምክንያት ያጣዉን የባህር በር ለማስመለስ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የብሪክስ አባል ሃገራት፤ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች፤ ምሁራን፤ ፖለቲከኞችና የህግ ተቋማት ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባታል በማለት እዉቅና እየሰጧት ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ130 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ብዛትና በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ያላት: በታሪክም ሆነ በአለም ህግ መሠረት በሠላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት መብት ያላት ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና አትኖርም ሲሉ መናገራቸዉ ይታወሳል።
በወንድማገኝ አሰፋ