AMN- መስከረም 23/2019 ዓ.ም
“ትንሿ ኢትዮጵያ” የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ፣ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መኖሪያነቷን በተግባር እያሳየች የዘንድሮውን የኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔን በድምቀት አስተናግዳለች።
የኦሮሞ ሕዝብ የሰላም፣ የምስጋና እና የአብሮነት መገለጫ የሆነው የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል፣ ባህላዊ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ በልዩ ድምቀት ተከብሮ ተጠናቋል። ይህ የደስታና የምስጋና በዓል በነገው ዕለትም በቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዴ በተመሳሳይ ድምቀት ይቀጥላል።
በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የምታስተናግደው የዲፕሎማሲ ማዕከሏ አዲስ አበባ፣ ከትናንት ጀምሮ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ኢትዮጵያውያንን ለኢሬቻ በዓል በአንድነት አሰባስባለች።
ልዩነት ውበቷ የሆነችው ኢትዮጵያ በልጆቿ ደምቃ ታይታለች። ከተማዋ በአምስቱም መግቢያ በሮቿ በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶቿን በታላቅ የኢትዮጵያውያን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል፣ በክብርና በፍቅር ተቀብላ አስተናግዳለች።
በሆረ ፊንፊኔ የኦሮሞ ሕዝብን ጨምሮ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በነቂስ የወጡ ሲሆን፣ የአንዱ ማኅበረሰብ ባህላዊ በዓል የሌላውም ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት መሆኑን በተግባር አንጸባርቀዋል።
ሥነ-ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ጭፈራ እና ውበት ደምቆ የታየበት ልዩ የኅብረ ቀለማት መድረክም ነበር።

ከኦሮሞ ማራኪ ባህላዊ አልባሳት ጎን ለጎን የሌሎች ማኅበረሰቦች አልባሳትም አብረው ደምቀው መታየታቸው እንዲሁም በተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎች መታጀቡ ኢትዮጵያዊ የኅብረ ብሔራዊነት እና የመከባበር እሴትን አጉልቶ አሳይቷል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ጠንካራ አንድነት ያላቸው፣ ልዩነታቸውን ደግሞ ውበት አድርገው የተቀበሉ መሆናቸውን ለዓለም በድጋሚ አስመስክረዋል።
“ኢሬቻ፡ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ የሚገኘው የዘንድሮው በዓል ትውፊቱን በጠበቀና ኢትዮጵያዊነትን በሚያስተጋባ መልኩ በድምቀት ቀጥሏል።
በትዝታ መንግስቱ