AMN – ጥቅምት 12/2019 ዓ.ም
በመዲናዋ የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት ለማሳደግ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቧል ሲል የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ገልጿል።
የዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለልና ፍትሃዊ የገበያ ሥርዓት ማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ አንዱ የትኩረት መስክ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምርቶችና በቤት ኪራይ ላይ የሚደረግ ምክንያታዊ ያልሆነ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪን ለመግታት፣ የታቀደ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ለመከላከል እና ህገወጥ ደላሎችን ከግብይት ሰንሰለቱ ለማስወጣት እየሰራ ያለውን ሥራ ለማጠናከር የሚያግዝ በየደረጃው ካለ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።
በተደረገው ውይይትና በውይይቱ የተቀመጡት አቅጣጫዎች በከተማዋ የኪራይና የግብይት ህጎች በህብረተሰቡ የነቃ ትብብር እንዲተገበሩ ፣ የሸማቾች መብት በተግባር እንዲከበርና በህገወጥ አሰራር ምክንያት የሚደርሰው የኑሮ ጫና እንዲቀንስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
በሰው ሰራሽ መንገድ የሚፈጠር የዋጋ ንረትና የዕቃ እጥረት የሸማቾችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከመጎዳቱም በላይ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱን ያናጋል።

በመዲናዋም መሰል ሁኔታዎችን የመፍታት አቅም የተፈጠረ ቢሆንም፥ አቅርቦትን ይበልጥ ለማሳደግና የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲያድግ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ገልጿል።
ከተማ አስተዳደሩ ህገወጥ ደላሎችን ከሰንሰለቱ በማስወጣት ከአምራች እስከ ሸማች ያለውን ሂደት ግልጽ ለማድረግ የወሰደው ውሳኔ ሸማቾች ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ የማግኘት መብታቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
በትግበራ ላይ ያሉ የኪራይና የግብይት ህጎች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እና ቁጥጥር ሲታከልበት በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪ መብቱን በማወቅ፣ ህገወጥ አሰራሮችን በመጠቆምና ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጽ/ቤቱ ገልጿል።
ይህ የተቀናጀ እርምጃ የአዲስ አበባን ሸማቾች ካልተገባ የዋጋ ጫና በመጠበቅ ረገድ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣና ጤናማ የከተማ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነውም ብሏል።