AMN – ጥቅምት 12/2019 ዓ.ም
በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ባሉ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች የተላለፉ ጠንካራ መልዕክቶች እና የታየው ሕዝባዊ ደጀንነት በመከላከያ ሠራዊትና በማሕበረሰቡ ዘንድ ያለውን ቁርኝት ያመላክታል።
የሀገር ሽማግሌዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ አደባባይ በመውጣት ለመከላከያ ሠራዊት እና ለሌሎች የፀጥታ አካላት ያሳዩት ድጋፍ ሕዝቡ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የሀገሩ ሉዓላዊነት እንዲከበር ያለውን መሻት ያንጸባርቃል።
ይህ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ የተገኘ፣ ለሕዝብ ብሔራዊ ፍላጎትና ደህንነት ዘብ የቆመ፣ የኢትዮጵያ ኅብረ-ብሔራዊነትና የአንድነት ሕያው አርማ መሆኑን አረጋግጧል።
ሠራዊቱ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ሲል የሚከፍለው ታላቅ ዋጋ በሕዝቡ ዘንድ የሚሰጠው ክብር ምን ያህል ጥልቅ እንሆነና ህዝቡ ለመከላከያው ደጀን መሆ ኑን በሰልፎቹ ተንጸባርቋል።
የውስጥና የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሐሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሕዝቡን ለማናወጥ፣ ለመከፋፈልና ሀገራዊ አንድነት ለማላላት ያደረጉት መፍጨርጨር መክሸፉን በሰልፎቹ የተላለፉት አቋሞች ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አንድነት በፀረ-ሰላም ኃይሎችና በታሪካዊ ጠላቶች አፍራሽ ሴራ እንደማይደናቀፍ ሕዝቡ በአንድ ድምፅ አረጋግጧል።
ሕዝቡ ለመከላከያ ሠራዊቱ፣ ለፌዴራልና ለክልል የፀጥታ ኃይሎች ያሳየው ወገንተኝነት የሠራዊቱን ቅቡልነትና ከሕዝቡ ጋር ያለውን ትስስር ማንም ሊበጥሰው እንደማይችል ያሳያል።

በሰልፎቹ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበርና ኢኮኖሚያዊ ግቦቿ እንዲሳኩ የተላለፈው መልዕክትም የኢትዮጵያንን መሻት ያንጸባረቀ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በራስ አቅምና የሕዝብ ተጋድሎ ለፍጻሜ ማብቃት እንደተቻለው ሁሉ ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር የማግኘት መብትንም እውን ለማድረግ ሕዝቡ ከመንግሥትና ከሠራዊቱ ጎን ለመሰለፍ ያለውን ዝግጁነት አሳይቷል።
ከግድቡ ወደ ወደቡ እንሸጋገራለን ፤ የባሕር በር ባለቤትነታችን በልጆቿ መሥዋዕትነትና በሕዝቧ አንድነት እውን ይሆናል! የሚለው የሰልፈኞቹ መልዕክት የኢትዮጵያ መሻት የማይቀለበስ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለው መሆኑንና ሕዝቡም ለሠራዊቱ ያለው አክብሮት፣ ፍቅርና ደጀንነት ይበልጥ እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል።
በታደሰ ሽፈራው