AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት በመከበር ላይ ይገኛል።
ቀኑ “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ እየተከበረ ነው፡፡
የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ ይከበራል።
ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን መከበር ከጀመረ 18 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነትና አስተባባሪነት በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
በዚህም መሠረት የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ዕለቱን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አማካኝነት በቀጥታ ስርጭት በመላው ሀገሪቱ ዜጎች በሠንደቅ ዓላማው ፊት ቃለ መሃላ የሚፈጸምበት ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ማርሽ ባንድ እና ክብር ዘብ ታጅበው በፕሬዘዳንቱ አማካኝነት ሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት፣ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ይህ በዓል በመላው ሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች እንደሚከበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።