በትግራይ ክልል ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም እና ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽኑ አስታወቀ

AMN – ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ሀገራዊ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ዲሞቢላይዝ የማድረግና መልሶ የማቋቋም (DDR) ፕሮግራም አተገባበርና አፈጻጸም ዙሪያ ከለጋሽ ሀገራትና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ዉይይት አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ92 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ ሀገራዊ ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር በርካታ ስኬታማ ተግባራትን ያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም አሁን ላይ በትግራይ ክልል በርካታ ታጣቂዎች ግጭትን በመተው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ለመመለስ በከፍተኛ ቁጥር ወደ ዲሞቢላይዜሽን ማዕከላት በመግባት በፕሮግራሙ ለመታቀፍ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ኮሚሽኑም የተጀመሩ ሥራዎችን በክልሉ አጠናክሮ ለማስቀጠል በአዲስ መልክ በተመረጡ ተጨማሪ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከላት የቀድሞ ተዋጊዎችን የመቀበልና በስልጠና ሂደቱ እንዲያልፉ የማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ሰላምን የማፅናት ተልዕኮም ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በከፍተኛ ቅንጅትና በትብብር እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ፕሮግራሙ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ፣ ከማኅበረሰባቸው ጋር በሰላም እንዲቀላቀሉና በሀገራዊ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሳተፉ ማድረግ በሀገር ማረጋጋትና በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

መንግሥት ለፕሮግራሙ ስኬት ከፍተኛ በጀት በመመደብ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የለጋሽ አካላት ተወካዮችም ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለማስቀጠልና ስኬታማ ለማድረግ ያሳየውን ተቋማዊ ጥረትና ቁርጠኝነት አድንቀው፣ ለፕሮግራሙ ዘላቂ ስኬት የሚያስፈልገውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ያላቸውን ሙሉ ዝግጁነት ማረጋገጣቸዉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review