AMN-ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ እውነተኛ አጋርነት ወሳኝ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስላለፉት መልዕክት ዛሬ የሚድሮክ ዐውደ ርዕይ ሳምንትን አስጀምረናል ብለዋል።

የግል ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን በሚያሣልጡ ዘርፎች ላይ እንዲሠማራ ማበረታታትና መደገፍ አንዱ የመደመር መንግሥት ተግባር መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም እንደ ሚድሮክ ያሉ ጠንካራ ሀገር በቀል ተቋማትን ማበረታታትና ዐቅማቸውን ማሳደግ ማለት የሀገርን ምርታማነት ማሳደግ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬና የግብር ገቢን ማሳደግ እንዲሁም የፈጠራና የቴክኖሎጂ ኀቅምን ማጠናከር ነው ብለዋል።

ሚድሮክ ከትናንት ስኬቶቹ ባሻገር፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ፣ በምርታማነትና በወጪ ምርት እንዲገነባ ጭምር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ፣ የተቋሙ ልምድና ዘመናዊ አሠራሮች ለሌሎች ሀገር በቀል ተቋማት ሲተላለፉ፣ የአንዱ ስኬት የብዙዎች የዕድገት መሠረት ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና በመንግሥት ጥረት ብቻ አይረጋገጥም፤ በግሉ ዘርፍእና በማኅበረሰቡ ጥረት ጭምር እንጂ።
በመንግሥት፣ በማኅበረሰቡና በግሉ ዘርፍ ጠንካራ አጋርነት፣ በጋራ ዐቅምና በጋራ ስኬት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እናረጋግጣለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡