ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተጻፈበት ነው – አፈ ጉባዔ አሕመድ ሺዴ

AMN- ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተጻፈበት ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ 19ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን እየተከበረ ይገኛል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሕመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የተጻፈበት፣ የጽናትና የጀግንነት ምልክት እንዲሁም የነጻነትና የሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ በሃገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ እንዳለው ገልጸዋል።

አፈ-ጉባዔው አሕመድ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹት፤ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነት እና ሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንድነት ማሳያ መሆኑ በሕግ በግልጽ ተደንግጓል።

በየዓመቱ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ የሚከበረው ይህ ብሔራዊ ቀን፣ ዘንድሮም አንድነታችንን፣ ጽናታችንንና አብሮነታችንን በሚያጸና መልኩ በጋራ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ይህንን ብሔራዊ በዓል በበላይነት የማስተባበር፣ የመምራት እና የሰንደቅ ዓላማን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን የማከናወን ታላቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው አፈ ጉባዔው ተናግረዋል።

አፈ-ጉባዔ አሕመድ ሺዴ አክለውም፤ ይህ ኃላፊነት የታሪክ፣ የሕዝብ እና የሕግ አደራ በመሆኑ ምክር ቤቱ በከፍተኛ ኩራትና ትጋት እየተወጣው እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review