AMN- ጥቅምት 2/2019ዓ.ም

ሰንደቅ ዓላማ የሕዝብ ማንነት፣ የነፃነት አየር፣ የታሪክ አሻራ እና የሚሊየኖች የጋራ ህልውና ውል ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለሞች ጥምረቱ የነፃነት ተምሳሌትነት ብቻ ሳይሆኑ፣ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የጽናትና የኩራት ምልክት በመሆን በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቅ የወርቅ ቀለም ተጽፏል።
ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸው ፍቅር በተራ ሀገራዊ ስሜት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ ቁርኝታቸውን በአብሮነትና በአንድነት ያጋመደ የህልውናም መሠረት ነው።
ሰንደቅ ዓላማ የሉአላዊነት ማረጋገጫ፣ የሀገር ዳር ድንበር መጠበቂያ እና በጠላት ፊት ኩራትን የሚያጎናጽፍ ታላቅ የክብር ካባ ምልክት ሆኖ ያገለግላል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ምንም እንኳን በመንግስታት ለውጥ ማዕከላዊ አርማዎቹ ቢቀያየሩም፣ ሦስቱ መሰረታዊ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለሞች ግን ሳይቀየሩ የኢትዮጵያዊነት ዘላቂ ምልክት ሆነው ቀጥለዋል።

ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለትና በነፃነት መውለብለብ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ትልቁንና የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
ለሰንደቅ ዓላማው ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ቃል ኪዳን የገባው መከላከያ ሰራዊት፣ ለሰንደቅ ዓላማው ክብር የከፈለውና እየከፈለ ያለው ዋጋ በታሪክ ተከትቦ ይኖራል።
በኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የታየው ጀግንነት፣ ሰንደቅ ዓላማዋ በዓለም ፊት የነፃነት ምልክት ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገ ነው፡፡
በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በሌሎች ሀገራት በተደረጉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችም፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ የዓለምን ሰላም ለማስከበር በላቀ ጀግንነት መስዋዕትነት መክፈሉ ታሪክ ምስክር ነው።
ከዚህም በላይ በየዘመናቱ የሚነሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሀገርን ለማፍረስና ሰንደቋን ለማዋረድ ሲደክሙ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዱር በገደሉ በመዋደቅ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ ሰንደቅ ዓላማው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በደሙና በአጥንቱ ያስከበረውን ሰንደቅ ዓላማ፣ የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ በስራ፣ በትምህርት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ከፍ አድርጎ የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የታሪክ እጥፋቶችን፣ የሥርዓት ለውጦችን እና በርካታ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰ የነፃነት አርማ ነው።
በወርቅነህ አቢዮ