AMN – ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልዕክት ፣ በሞስኮ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገኘት መልዕክቴን ማስተላለፍ በመቻሌ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
በዚህ ታሪካዊ መድረክ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የጋራ ቁርጠኝነት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እነዚህም በምግብ ዋስትና እና ምርታማነት፣ በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ እንዲሁም በክህሎት እና በዕውቀት ሽግግር ላይ የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የጸና ታሪካዊ ወዳጅነት መሆኑንም በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

ይህንን ወዳጅነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከሩሲያ ጋር በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት እያከናወንን እንገኛለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
ይህ ስትራቴጂካዊ ትብብር የኃይል አማራጮቻችንን ከማስፋት ባለፈ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ትስስር ከምንጊዜውም በላይ የሚያጠናክር ይሆናል ብለዋል።