AMN- ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም
የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን እንዲሁም የሁለቱ አህጉራት አባል ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት የሁለትዮሽ የምክክር ስብሰባ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት መካሄድ ጀምሯል።
ይህ ስብሰባ በጋራ የትብብር ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር እና በጋራ ትኩረት በሚሹ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ቅንጅትን ለማጠናከር ያለመ ትልቅ መድረክ ነው።
ስብሰባው እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2025 በሉአንዳ «ውጤታማ በሆነ ባለብዙ ወገን ትብብር ሰላምና ብልፅግናን ማጎልበት» በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን 7ኛውን የአፍሪካ-አውሮፓ ኅብረት ጉባኤ ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው።
በሉአንዳ ጉባኤ የተገቡ ቃሎችን መሠረት በማድረግ፣ የስብሰባው ዋና ትኩረት በባለብዙ ወገን ትብብርና በብልፅግና ዙሪያ ባሉ ሀገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
ስብሰባው በሰላምና ደህንነት፣ በባለብዙ ወገን ትብብር ማጠናከር፣ በንግድና ኢኮኖሚ ልማት፣ በካይ አየር ለውጥ፣ በምግብ ዋስትና፣ በዲጂታልና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ልማትና አስተዳደር ዙሪያ ትብብርን ለማስፋት የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራት ያካተተ የተግባር ዕቅድ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ዕቅድ የ2030 የጋራ ራዕይን እንዲሁም አጀንዳ 2063 እና «ግሎባል ጌትዌይ» (Global Gateway) የተሰኙ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፎችን እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው።
ስብሰባው የሉአንዳውን ጉባኤ ውሳኔዎች ወደ ተጨባጭና ውጤት ተኮር ተግባራት በመቀየር የአፍሪካና የአውሮፓ ሕዝቦችን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶችና ድርድሮች የተዘጋጀ ነው።
በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ቻምፒዮን ባላቸው ኃላፊነት መሠረት፣ በዲጂታልና የሰው ሠራሽ አስተውሎት አስተዳደርና ልማት ዙሪያ የአፍሪካን የጋራ አቋም አቅርባለች።
አምባሳደር ለምለም ፈሰሃ የቻምፒዮኑን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎትና ዲጂታላይዜሽንን በአባል ሀገራት የፖሊሲ ቅድሚያዎች ውስጥ ማካተት፣ ሁለንተናዊ የዲጂታል እውቀትን ማረጋገጥ፣ በሳይበር መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣ ለዲጂታል ስታርት አፖች (ጀማሪ ድርጅቶች) ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የአፍሪካ ቋንቋዎች በዲጂታል ዓለም የሚያደርጉትን ተሳትፎ ማጎልበት እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተጽዕኖዎች የመቆጣጠር አቅምን መገንባት ዋና ዋና ትኩረቶች ናቸው።

በሌላ በኩል፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር መለስ ዓለም የተወከለችው ኢትዮጵያ፤ በአፍሪካና አውሮፓ ኅብረት መካከል በንግድ፣ በኃይል ልማት እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ትብብርን ማስፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ አብራርታለች።
አምባሳደር መለስ የአውሮፓ ኅብረት ከጦር መሣሪያ በስተቀር ሁሉም ነገር የተሰኘውን የታሪፍ ነፃ ንግድ ድጋፍ ትግበራ ላይ ያሉ ማቅለሎችን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተለይም የደን ጭፍጨፋን ለመግታት የወጡ አሰራሮችን እና የካርቦን ድበር ማስተካከያ አሰራርን መሻር ወይም ማስተካከል እንደሚገባ ጠቅሰው፣ እነዚህ መመሪያዎች በአፍሪካ የኮኮዋ፣ የቡና እና የሌሎች ስልታዊ ምርቶች አምራቾች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አስረድተዋል።
በኃይል ዘርፍም አምባሳደር መለስ የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካ ኅብረት የፒዳ (AU-PIDA) ፕሮጀክቶች ላይ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡