የመደመር እሳቤ በተግባር የተገለጸባት እና የኅብረብሔራዊ ወንድማማችነት ማዕከል – አዲስ አበባ

You are currently viewing የመደመር እሳቤ በተግባር የተገለጸባት እና የኅብረብሔራዊ ወንድማማችነት ማዕከል – አዲስ አበባ

AMN – ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም

የመደመር እሳቤ በሀገራችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጽታዎች ላይ አዲስ ምዕራፍ ያስተዋወቀ ታላቅ ንድፈ-ሐሳብ ነው። ይህ እሳቤ ልዩነቶችን አቻችሎ፣ ያለፉትን ክፍተቶች በመሙላት፣ በጋራ ሀብትና ዕውቀት ላይ በመመስረት የጋራ የድል አድራጊነት ማማ ላይ ለመድረስ ያለመ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት ጥቂት ዓመታት ያስመዘገባቸው ግዙፍ ሁለገብ ለውጦች የመደመር እሳቤ በተጨባጭ መሬት ወርዶ የህዝብን ሕይወት እንዴት እንደቀየረው ሕያው ማሳያዎች ናቸው።

አዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት ያከናወነችው የኮሪደር ልማት ስራ የትብብር እና የዕይታ አንድነት ውጤት ነው። የመንገድ መሠረተ ልማቶች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መተላለፊያዎች እና ዘመናዊ መብራቶች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪስቶች ማራኪ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።

ህብረተሰቡ ነፃ አየር የሚተነፍስባቸው፣ የኢኮሎጂ ሚዛንን የጠበቁ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች እና በባህላዊ መስተጋብር የሚጎለብቱባቸው የጋራ ቦታዎች መገኛ ሆናለች። እነዚህ ቦታዎች የመደመር እሳቤ ማህበራዊ ፍትህንና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ያለውን አቋም በግልጽ ያሳያሉ።

አዲስ አበባ ከነባር እሴቶች ጋር ተስማምቶ ወደፊት መራመድን አሳይታለች። የከተማዋ አስተዳደር የኢትዮጵያን አርበኝነት፣ የአፍሪካ ነጻነት ፋና ወጊነት እና የጥቁር ህዝቦች ኩራትን የሚያሳይ ግዙፍ ታሪካዊ ማዕከል የሚያሳይ እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ በመገንባት፤ የጋራ ታሪካችንን በማክበር ላይ የተመሰረተውን የመደመር እሳቤን በተግባር ያንጸባርቃል።

አዲስ አበባ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚገናኙባት የባህል መስተጋብር ማዕከል ናት። ማህበራዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች በድምቀት የሚከበሩባት፣ የመደመር እሳቤ የልዩነት ውበትን ወደ አንድነትና ወንድማማችነት በይፋ የምታስመሰክር ከተማ ናት።

የመደመር እሳቤ በምጽዋት ላይ የተመሰረተ ልማት ሳይሆን፣ አቅምን አቀናጅቶ በራስ መተማመን ላይ የቆመ ምርታማነትን ያነግሣል። በከተማዋ የተከናወኑ የግብርና፣ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፎች፣ እንዲሁም ዘመናዊ የዲጂታል አሰራር ሽግግሮች የዜጎችን ተጠቃሚነት አረጋግጠዋል።

ወጣቶች፣ ሴቶች እና አቅመ-ደካሞች የልማቱ ባለቤት እንዲሆኑ የተደረጉ ስራዎች የመርሁ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

የመደመር እሳቤ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ የከተማዋን መልክ የቀየረ፣ የህዝቡን የኑሮ ማዕቀፍ ያሻሻለ፣ ታሪክን ከዘመናዊነት አስተሳሰር ጋር ያዋሃደ እና የጋራ ኑሮን ያጸና የተግባር ማሳያ መድረክ መሆኑን አዲስ አበባ በግልጽ አስመስክራለች።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review