ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ያላት ሚና

You are currently viewing ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ያላት ሚና

AMN- ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምን፣ ዲሞክራሲን እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ የምክክር እና የትብብር መድረክ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ. በኦገስት 2025 በጋና አክራ የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ፣ የፖለቲካ ሃይሎች ትኩረታቸው ከምርጫ ፖለቲካ ባሻገር እንደ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ባሉ አህጉራዊ የልማት ግቦች ላይ መሆን እንዳለበት መሰረት የጣለ ነበር።

በዚሁ የመጀመሪያ ስብሰባ በገዥና ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የጋራ ትብብርን ማጠናከር፣ የሴቶችን እና የወጣቶችን ውሳኔ ሰጪነት ማሳደግ፣ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን ማክበር እና የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጠናን በፖለቲካ ቁርጠኝነት መደገፍ የሚሉና ሌሎችንም ሀሰቦችን ያካተተ ባለ 10 ነጥብ መግለጫዎች ወጥተዋል፡፡

የመግለጫው ዋና አላማ የፓርቲዎችን ተቋማዊ አቅም መገንባት፣ የልማት ፖሊሲዎችን ማስተጋባት እና የትብብር ባህልን ማጎልበት ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ከተቀመጡት አቅጣጫዎች መካከል አብዛኞቹን ነጥቦች በተግባራዊ እንቅስቃሴዎቿ፣ በህጋዊ ሪፎርሞቿ እና በፖለቲካዊ እርምጃዎቿ በማሳካት ረገድ ረጅም ርቀት ተራምዳለች።

ኢትዮጵያ የአክራውን መግለጫ በተግባር እየተረጎመች ያለች ሀገር ናት።

በመጀመሪያ ደረጃ ፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ስልጣን በማጋራት በሃገራዊ ጉዳይ ተቀራርቦ መሥራት የሚያስችል መደላድል ፈጥራለች።

ሀገሪቱ በታሪኳ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ያቋቋመችው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና ተጠናክሮ የቀጠለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክም ቀዳሚ ማስረጃዎች ናቸው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የወጣቶችንና ሴቶችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት በውሳኔ ሰጪነት ተሳትፏቸውን አሳድጋለች።

የሴቶች ስብጥርን በመጠበቅ እና በርካታ ወጣት አመራሮችን ወደ ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪነት በማምጣት ከአፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።

በሦስተኛ ደረጃ ፣ የ10 ዓመቱን የመሪ ልማት ዕቅድ በመቅረጽ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በሌማት ትሩፋትና በከተሞች ኮሪደር ልማት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063ን አህጉራዊ ራዕይን ያገናዘቡ ናቸው።

በተጨማሪም የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጠናን ከመደገፍ አንጻር ስምምነቱን ማጽደቋ ብቻ ሳይሆን የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግንና የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡

የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለፖለቲካዊ ተሳትፎ የመጠቀም መመሪያንም በ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እና በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የዲጂታል አሰራር አረጋግጣለች።

ህገ-መንግስታዊነትን እና የህግ የበላይነትን ለማጠናከር እንደ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያሉ የዲሞክራሲ ተቋማት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው በገለልተኝነት እንዲሰሩ የተደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ኢትዮጵያ የመግለጫውን ውሳኔዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ ያሳየችውን ቁርጠኝነት ያመላክታል።

ኢትዮጵያ የአክራ መግለጫን በማሳካት ያሳየችው ይህ ተጨባጭ ቁርጠኝነት እና ያበለጸገችው ሀገራዊ ተሞክሮ፣ ሁለተኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንድታዘጋጅ ከተመረጠችባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው።

በተጨማሪም አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መሪያ ቤት እንዲሁም በርካታ ኤምባሲዎች የሚገኙባት የአህጉሪቱ ዋና የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗ 2ኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንድታዘጋጅ አስችሏታል፡፡

በኮንፈረንስ መሰረተ-ልማት አቅም ረገድም ስብሰባው የሚካሄድበት ዘመናዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮንፈረንስ ማዕከል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አህጉራዊ የትራንስፖርት ትስስር እንግዶችን በከፍተኛ ደረጃ ለማስተናገድ የሚያስችሉ በመሆናቸው ከተማዋ ቀዳሚ ምርጫ ልትሆን ችላለች።

በዚህም መሰረት ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2019 ዓ.ም ሀሳብ ይካሄዳል።

ጉባኤው በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቅረፅ፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ያላቸውን ሚና በማጎልበት፣ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ እንቅፋቶችን በማስወገድ፣ አካታች አስተዳደርን በማስፈን እና የፓርቲዎችን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መልዕክቶችን በማውጣት አህጉራዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አቅጣጫን በግንባር ቀደምትነት ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review