AMN – ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ታሪካዊ ግንኙነታቸውንና ወታደራዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ከውጭ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር የሚያደርጉትን ተከታታይ የወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውይይት በመቀጠል በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረውን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግና በወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።
በውይይቱ አቶ መሐመድ እድሪስ፤ ለፈረንሳይ አሁናዊ እና ስትራቴጂያዊ ወታደራዊ አቅምን ለማሳደግ እያደረገች ላለችው የዕውቀት ሽግግር እና የሰላም ማስከበር ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋማ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጠናው ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ጥቅሟን ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት ፈረንሳይ ከጎኗ እንድትቆምም ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን የትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም(DDR) ሂደት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ፈረንሳይ ለሂደቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነትና ሁለገብ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አሳውቃለች።

በተለይም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም በወታደራዊ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ዘርፎች የሚከናወኑ የጋራ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።