AMN- ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም
የአፍሪካ የኢኮኖሚ መጻኢ ዕድል ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው የያዝነውን ሀገራዊ አቅም ወደ እውነተኛ እና ውጤታማ አቅም መቀየር በሚቻልበት ቁመና ላይ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም ፋራህ፤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም፤የፖለቲካ ኃላፊነት ሁልጊዜም የልማት እና የዕድገት ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ይህንን ታሪካዊ ሀገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ የሚገኘው የፓርቲው ፕሬዚዳንት በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተቀረጸው የመደመር ሀገር በቀል ፍልስፍና ላይ በመመሥረት መሆኑን አንስተዋል፡፡

መደመር ሰዎችን፣ ተቋማትን እና ስኬቶችን በጋራ ዓላማ ዙሪያ በማሰባሰብ መከፋፈልን የሚያሸንፍ እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚገነባ የለውጥ ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው የሰብአዊ ክብርን፣ ፀጥታን፣ የኢኮኖሚ ዕድልን እና ማኅበራዊ ደኅንነትን የሚያረጋግጥ ውጤታማ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥብቅ ቁርጠኝነት እንዳለው ያነሡት አቶ አደም ፋራህ፤ አሁን ላይ ፓርቲው ወደ 17 ሚሊየን አባላት እና ጠንካራ ሀገር አቀፍ መዋቅሮች ያሉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም እና ለልማት ግልጽ አቅጣጫ ሊሰጡ፣ ኢንቨስትመንትን ማሰባሰብ፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ማዳበር እና በትውልዶች መካከል ያለውን ዕድገት የሚያስቀጥሉ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አካታች ፖለቲካን እውን ለማድረግም ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተውጣጡ ከ275 በላይ መሪዎችን በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ላይ በመመደብ የጋራ ሀገራዊ አደራ ማጠናከር መቻሉን ገልጸዋል።