አዲስ አበባ፡ የአፍሪካውያን የከፍታ ማዕከል

You are currently viewing አዲስ አበባ፡ የአፍሪካውያን የከፍታ ማዕከል

AMN – ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም

የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት፣ ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና ለተቋማዊ መልካም አስተዳደር መሠረት የመሆን ድርሻቸው ከፍተኛ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ፍላጎት ከመወከልና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ከመቅረጽ አልፈው፣ የአህጉሪቱን የተበታተነ ሀብት፣ የሰው ኃይል እና የጂኦ-ፖለቲካዊ አቅም አስተባብረው ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የመቀየር ታሪካዊና መዋቅራዊ ኃላፊነት አለባቸው።

ይሁን እንጂ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ራሳቸውን እንደ ዋነኛ የልማትና የለውጥ ኃይል አድርገው የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጥረት አጋጥሟታል።

በአህጉራዊ ደረጃ የተቀናጀ የልማትና የታላቅነት ርዕይ ይዞ ባለመቆሙ ምክንያት አፍሪካ ከፍተኛ አህጉራዊ ኪሳራዎችን አስተናግዳለች።

አፍሪካ አንድ ካልሆነችና በጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅጣጫ ካልተመራች፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በርካሽ እየሸጠች የካፒታልና የቴክኖሎጂ ጥገኛ ሆና እንድትቀር ያደርጋታል።

በመሆኑም ያለፉትን ክፍተቶች በማረም በአህጉሪቱ በሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የፖሊሲ ልውውጥ ማድረግ፣ በፋይናንስ አስተዳደር ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማሰፈን፣ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና ዘመናዊ አስተዳደርን መገንባት ለአህጉራዊ ከፍታ ወሳኝ ነው።

ይህን መዋቅራዊ ክፍተት ለመሙላት የታለመው ታላቅ አህጉራዊ ጉባኤ “የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና” በሚል ጭብጥ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ይህ ታላቅ ጉባኤ፣ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱ የፖለቲካ ማዕከልነቷን፣ ታሪካዊ ውርሷን እና እያስመዘገበች ያለችውን ዘመናዊ የልማት ስኬት የሚመሰክር ነው።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ከፍታ፣ ለነጻነት፣ ለጸረ-ቅኝ ግዛት ትግል እና ለጥቁር ሕዝቦች ኩራት አምሳል ሆና የቆየች ሀገር ናት።

በተለይም በ1888 ዓ.ም የተጎናጸፈችው የዓድዋ ድል አፍሪካውያን ቅኝ ገዥ ኃይሎችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያረጋገጠ፣ የአፍሪካ ብሔረተኝነትና የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንዲወለድ መንገድ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት ነበር። የዓድዋ ድል ለአፍሪካ ህብረት መሠረት ለሆነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መወለድ እና ለአዲስ አበባ የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማነት መሠረት ጥሏል።

ለዚህ ጉባኤ መሰብሰቢያነት የተመረጠው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ደግሞ በራሱ ጥልቅ የሆነ ተምሳሌታዊ ትርጉም ያለው ነው።

መታሰቢያው አፍሪካውያን በአንድነት ቆመው የተጎናጸፉትን አንጸባራቂ ድል የሚዘከርበት ቦታ ከመሆኑም በላይ፣ አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያረጀ ገጽታዋን አውልቃ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ በዲጂታል አሠራር እና በቱሪዝም መሠረተ ልማት በመደመር እሳቤ መሠረት ላይ ቆማ እያሳየች ያለችው ፈጣን እድገት፣ አህጉራዊ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ እጅግ ምቹ ምህዳር ስለመፈጠሩም የሚያሳይ ነው።

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review