አፍሪካዊ ህዳሴ፣ አህጉራዊ አንድነት እና የፖለቲካ ትብብር አዲስ ምዕራፍ

You are currently viewing አፍሪካዊ ህዳሴ፣ አህጉራዊ አንድነት እና የፖለቲካ ትብብር አዲስ ምዕራፍ

AMN- ጥቅምት 29/2019 ዓ.ም

አፍሪካ ዛሬ በታሪካዊ የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች። የኢኮኖሚ ነፃነቷን ለማረጋገጥ፣ የቴክኖሎጂ አቅሟን ለመገንባት እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ ባደረገችው ርብርብ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ነው።

2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤም አህጉሪቱ መጻኢ ዕጣ ፈንታዋን በውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ሳይሆን በራሷ ለመወሰን ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያረጋገጠችበት ታላቅ መድረክ ሆኗል።

የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ብርሃን አብነቷ ኢትዮጵያ ዛሬም ለአህጉራዊ ትንሣኤ ግንባር ቀደም መሪ መሆኗን አስመስክራለች።

ከአፍሪካ ማዕዘናት የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሙድ አሊ ዩሱፍ በተገኙበት የተካሄደው ይህ ጉባኤ፤ የአፍሪካ ትብብር ከወረቀት አልፎ በእጅ የሚዳሰስ እውነት መሆኑን አሳይቷል።

ኢትዮጵያ ለዘመናት የያዘችውን የነፃነትና የትብብር መንፈስ በድጋሚ በዚሁ ጉባኤ ላይ አስመስክራለች። አሁን ላይ አፍሪካውያን መሪዎች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው የብሩህ ዕጣ ፈንታቸው ላይ መወያየታቸው፣ የቅኝ ግዛት አባዜንና የዘመናት ክፍፍሎችን ሰብሮ በመውጣት ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ ነው።

አፍሪካ ለረጅም ዘመናት በውጭ እርዳታና በውጭ አቅጣጫ የምትመራበትን የጥገኝነት ምዕራፍ በራሷ ልጆችና በራሷ አቅም አመራር እየቀየረችው ትገኛለች።

አህጉሪቱ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ ለራሷ ችግሮች በራሷ አመራሮች፣ በራሷ ሀብት እና በባለሙያዎቿ አቅም መፍትሔዎችን ማመንጨት እንደምትችል በተግባር እያረጋገጠች ነው።

ለዚህ ታላቅ ዓላማ መሳካት እና አህጉራዊ ትብብርን ተቋማዊ ለማድረግ የተቋቋመው ‘የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ’ የዚህ ጥረት አንዱ ተግባራዊ ማሳያ መሆኑን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንን ወሳኝ ኢኒሼቲቭ ብልፅግና ፓርቲ እንዲመራ መወሰኑ ደግሞ ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መርሆች የሰጠችውን ታሪካዊ ቀጣይነት እና አርአያነት በድጋሚ ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የጸደቀው ‘የአዲስ አበባ ቃል ኪዳን’ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ትብብር ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው።

ይህ ታላቅ ጉባኤ አፍሪካ አህጉራዊ ሉዓላዊነቷን አጽንታ፣ መጻኢ ጊዜዋን ዕጣ በራሷ እጅ ይዛ ወደ ላቀ የብልጽግና ከፍታ እየተጓዘች መሆኗን ለመላው ዓለም ያበሰረበት እና ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሠረት የጣለ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ በስኬት ተጠናቅቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review