ዓባይ መፍሰሱን አያቆምም፤ ኢትዮጵያም ከቀይ ባሕር አትነጠልም

You are currently viewing ዓባይ መፍሰሱን አያቆምም፤ ኢትዮጵያም ከቀይ ባሕር አትነጠልም

AMN- ጥቅምት 29/2019 ዓ.ም

የዓባይ ወንዝ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር ለመፍሰስ ማንንም ፈቃድ ጠይቆ አያውቅም፤ ወደፊትም አያቆምም።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የኢትዮጵያ እና የቀይ ባህር ቁርኝት የታሪክ፣ የጂኦግራፊ እና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በምንም አይነት ጊዜያዊ ተፅዕኖና ጫና የሚቋረጥ ወይም የሚቆም አይደለም።

በአፍሪካ በኢኮኖሚና በህዝብ ቁጥር ከሚጠቀሱ ግዙፍ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያን የባህር በር መውጫ እንዳይኖራት መደረጉ መልክአ ምዳራዊውን ተፈጥሯዊ ሚዛን ያዛባል።

የኢትዮጵያ እና የቀይ ባህር ቁርኝት በጊዜያዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ሊደመስስ የሚችል አይደለም። ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ እስከ 20ኛው ምዕተ ዓመት ማገባደጃ ድረስ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ነበረች ፤ በባህር ንግድ እና በጂኦፖለቲካዊ ግንኙነት ዓለምን ስታስተሳስር ቆይታለች።

የባህር በሯን በሴራዎች ተነጥቃ መቅረቷ ጊዜያዊ ማጣቷ እንጂ የዘላለም እጣ ፈንታዋ አይደለም። ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ቁርኝት ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ህጋዊ መሠረት ያለው ነው።

የቀይ ባህር አካባቢ ዋናው የምግብ ዋስትና፣ የንግድ መስመር እና የጂኦፖለቲካ ተደራሽነት ከኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው።

ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓባይ ውሃ አመንጭታ ለሰሜን አፍሪካ ስትሰጥ የኖረች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ስትገነባ፣ ዓባይን አስቀርታ ልታጠፋን ነው በሚል ሃሳዊ ሙሾ ልማቷን ለማደናቀፍ ያልተዘረጋ ወጥመድ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያውያን አሉባልታውን ሁሉ ድል ነስተው ግዱቡን እውን አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን አረጋገጠች እንጂ ሌሎችን ስለመከልከልና ለመጉዳት አስባም አታውቅም፡፡ ዓባይም ተፈጥሯዊ ፍኖቱን ጠብቆ መጓዙን አላቆመም፡፡ የህዳሴ ግድብም እውን ከመሆን ማንም አልገታውም፡፡ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄም እንዲሁ ማንም ሊያፍነው አይችልም፡፡

የዓባይ ወንዝ ውሃ ወደ ግብጽና ሱዳን መፍሰሱን እንደማያቆም ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ከቀይ ባህር ተነጥላ ለዘላለም አትኖርም። እነኚህ ሁለት ግልጽ ሃቆች ናቸው፡፡ የሚያዋጣው ለኢትዮጵያ ቀና ጥያቄ ተባባሪ ሆኖ ተገቢ ምላሽ መስጠት ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሰላም፣ የትብብር እና የጋራ ዕድገት መንገዶችን ብትመርጥም ከቀይ ባህር ጋር ያላትን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብት የሚነፍግ አካሄድ አሜን ብላ አትቀበልም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት፣ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብን የመልክአ ምድር እስረኛ አድርጎ መቀጠል የሚቻል አይደለም፡፡

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ እያደረገች ላለቻቸው ዲፕሎማሲያዊና የጋራ የኢኮኖሚ ትስስር ጥረቶች እና የሰላማዊ ትብብር መንገዶች አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ለቀጣናው ብልጽግና እና ሰላም ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review