AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተገነቡት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች የተገልጋዩን እንግልት የሚቀንሱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር አያልነሽ ሃ/ማርያም ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ሥርዓትን ወደ ተቀናጀና ዘመናዊ አሠራር የሚያሸጋግሩ መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ኢንጂነር አያልነሽ ሃብተ ማርያም እንደገለጹት፤ አዲስ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና ተርሚናሎች የህብረተሰቡን እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱ ናቸው።
እያንዳንዳቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁ፣ ሙሉ በሙሉ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ልዩ ምቾትን የሚያጎናጽፉ ናቸውም ብለዋል፡፡

በውስጣቸው የታክሲ እና አውቶብስ ተርሚናሎች፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጀሮች እንዲሁም የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ተካተዋል።
በተጨማሪ የንግድ ሱቆች፣ ካፊቴሪያ እና ሬስቶራንቶች፣ የልጆች መጫወቻ እና ማረፊያ ስፍራዎች እንዲሁም ምቹ የተሳፋሪ መጠበቂያ ስፍራዎች ተሟልተዋል።
ተርሚናሎቹ አሳንሰሮችን እና ንጹህ መጸዳጃ ቤቶችን እንዲሁም የደህንነት እና አደጋ ቅድመ መከላከያ ስርዓቶችን ያካተቱም ናቸው፡፡
ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ አገልግሎት ሲገቡ በከተማዋ ጤናማ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የተሽከርካሪ ፍሰት እና የእግረኛ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከማስቻላቸውም ባሻገር ለከተማዋ የ«ስማርት ሲቲ» ውጥን እውን መሆን ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
በወርቅነህ አቢዮ