AMN -ጥቅምት 30/2019
ኢትዮጵያ በCOP31 ላይ የምታደርገው ተሳትፎ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መድረክ ላይ የምታሳየው ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን፣ ለCOP32 አዘጋጅነት ያበቋትን የልማት ስኬቶች፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እርምጃዎችና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተከተለች ያለውን ተግባራዊ አቅጣጫ ለዓለም የምታስተዋውቅበት ታላቅ አጋጣሚ ነው።
የCOP32 (Conferance of Parties – 32) አስተናጋጇ መዲና አዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የCOP31 ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ቱርክ፡ አንታሊያ ገብተዋል፤
ከንቲባ አዳነች በአንታሊያ ቆይታቸው ከተለያዩ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪ ቡድኖች እና ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቱርክዋ አንታሊያ በፈረንጆች አቆጣጠር ከህዳር 9 እስከ 20 ቀን 2026 በሚካሄደው COP31 ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የCOP32 አዘጋጅ አገር እንደመሆኗ የምትወስዳቸው ግብዓቶች በቀጣይ የሚኖራትን ዝግጅት ከማጠናከር ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድሮች፣ በአረንጓዴ ፋይናንስ ማሰባሰብ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በንጹህ ኃይል ልማትና በአየር ንብረት መቋቋም አቅም ግንባታ ዙሪያ ያላትን ልምድና አቅም እንድታሳድግ ዕድል ይፈጥራል።
በተለይም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በደን ልማትና ጥበቃ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና በአየር ንብረት ተቋቋሚ ልማት ዘርፎች እያከናወነች ያለቻቸው ሥራዎች በCOP31 ላይ በተግባር ለዓለም ሊቀርቡ የሚችሉ ተሞክሮዎች ናቸው።
አዲስ አበባም የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያደረገችውን ከፍተኛ አስተዋጾኦ ለሌሎች ሀገራት ልምዷን ታካፍላለች፡፡
የCOP32 አስተናጋጇ አዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤም በውይይታቸው በአዲስ አበባ በቀጣይ የሚካሄደው COP32 አካታች፣ በተግባር ላይ ያተኮረና ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኝ እንዲሆን የጋራ መግባባትን እና ትብብርን ለማጠናከር ያለሙ እና ከCOP31 ወደ COP32 የሚደረገውን ሽግግር በተሳለጠ ሁኔታ ለማስቀጠል ትኩረት በማድረግ ነው፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጋር የምትታገል አገር ብቻ ሳትሆን፣ ለችግሩ መፍትሔ በማበርከት የራሷን ልምድና መፍትሔዎች ለዓለም ማካፈል የምትችል አገር መሆኗን ለማሳየት ያስችላል።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባም የአገሪቱን ስኬት በከተማ ልማት ዘርፍ የምታስመሰክርበት ወሳኝ መድረክ ይሆናል።
በወንዞች ዳርቻ ልማት፣ በኮሪደር ልማት፣ በከተማ አረንጓዴነት፣ በዘመናዊ የትራንስፖርት መሠረተ ልማትና በሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ እየተከናወኑ ያሉት ለውጦች ከከተማ ውበት ባለፈ የአካባቢ ጥበቃን፣ የኑሮ ጥራትንና ዘላቂ የከተማ ልማትን ያማከሉ ተግባራዊ ምሳሌዎች ናቸው።
አዲስ አበባ የወንዞቿን ዳርቻዎች ከብክለትና ከተፈጥሮ አደጋ ስጋት ወደ አረንጓዴ መዝናኛ፣ የስፖርት፣ የቱሪዝምና የማኅበራዊ ትስስር ማዕከላት እየቀየረች መሆኗ፣ የኮሪደር ልማቷም ዘመናዊ መሠረተ ልማትን ከአረንጓዴ ስፍራዎችና ከሰው ተኮር የከተማ አገልግሎት ጋር አቀናጅቶ እያስፋፋ መሆኑ ለዓለም የሚቀርቡ ጉልህ ተሞክሮዎች ናቸው።
ይህም አረንጓዴ ልማት ከኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ከዜጎች የኑሮ ጥራት ጋር ተቀናጅቶ ሊሄድ እንደሚችል የሚያሳይ ተግባራዊ ምሳሌ ነው።
ኢትዮጵያ የCOP32 አዘጋጅ አገር እንድትሆን መመረጧም ከአንድ የጉባኤ አዘጋጅነት ኃላፊነት በላይ ትርጉም አለው።
ይህ ምርጫ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላትን ሚና፣ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫዋንና ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማዘጋጀት ልምዷን የሚያንጸባርቅ እድል ነው።
በተለይም በ2025 የሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ማስተናገዷ ለዚህ አዲስ ኃላፊነት ያላትን የዝግጅትና የትብብር ልምድ የሚያጠናክር ነው።
በመሆኑም COP31 ኢትዮጵያ ከዓለም ለመማር፣ አዳዲስ የትብብር አጋሮችን ለማፍራት፣ የአየር ንብረት ፋይናንስና ቴክኖሎጂ ተደራሽነቷን ለማሳደግ እንዲሁም ለCOP32 የምታዘጋጀውን አጀንዳ ለማጠናከር የሚያስችላት ወሳኝ የዝግጅት መድረክ በመሆኑ፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የCOP32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) እና ሌሎችም ልኡካን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ውይይቶችን እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በተመሳሳይም ኢትዮጵያና አዲስ አበባ በልማት፣ በአረንጓዴነትና በዘላቂ ከተማ ግንባታ የተመዘገቡ ለውጦቻቸውን ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ታላቅ ዕድል መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።
የCOP32 አዘጋጅነት ማለት ዓለምን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት ጥያቄዎች፣ የመፍትሔ ሐሳቦችና የልማት ተሞክሮዎች በዓለም አቀፍ ውይይት ውስጥ የበለጠ ቦታ እንዲያገኙ ማስቻልም ጭምር ነው።
ስለዚህ ከCOP31 የምንወስደው ተሞክሮና ግብዓት ለCOP32 ዝግጅት መሠረት ሲሆን፣ በCOP32 የምናቀርበው ደግሞ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የተግባር ስኬት፣ ምኞትና የወደፊት ራዕይ ይሆናል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት፤ በመደመር እሳቤ በመመራት የአረንጓዴ ልማት ስራዎቿ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንደሚቻል በአለም አቀፍ መድረኮች ያሳየችው ሀገራችን ከCOP31 ተሞክሮ ወደ COP32 ዓለም አቀፍ አጀንዳ፤ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ ወደ ዓለም የጋራ መፍትሔም ትሸጋገራለች!