AMN- ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

በሽታን መከላከል የሚቻለው የመሠረተ ልማት እና የምግብ ዋስትና ችግሮች ሲቀረፉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ዘመኑ የደረሰበትን የሕክምና ጥበብ አሟልቶ የተገነባውን እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀውን የላፍቶ ሆስፒታል መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን በስፋት ማከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በሽታን መከላከል ከመሠረተ ልማት ይጀምራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለእግር ጉዞ የሚመች መንገድ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የሕፃናት መጫወቻ ሜዳ በሌለበት ከተማ ውስጥ በሽታን ሙሉ በሙሉ መከላከል አይቻልም ብለዋል፡፡
እነዚህ መሠረተ ልማቶች ሳይሟሉ ሲቀሩ ወጣቶች ወደ አልባሌ ቦታዎች፣ አዛውንቶች ደግሞ ለደኅንነት እጥረትና ለብቸኝነት እንደሚጋለጡ ጠቁመው፣ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ የበሽታ መከላከያ ዋነኛ መንገድ መሆኑንም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የራበው ሰው በሽታን መከላከል አይችልም፤ በሽታ ልክ እንደ ጦር ውጊያ ትጥቅ ይፈልጋል፣ ትጥቁ ደግሞ ምግብ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት የመመገቢያ ማዕከላትና የማዕድ ማጋራት ልማዶችም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ሙከራዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
በጤናውና በትምህርት ዘርፍ ያሉ ማኅበራዊ ክፍተቶችን በመንግሥት ብቻ መፍታት እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ሆስፒታል ለመገንባት ቢፈልጉም በቦታ እጥረትና በድጋፍ ማጣት መቸገራቸውንም ጠቅሰዋል።
ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ የግል ሆስፒታሎችን በመጎብኘት የሚጎድላቸውን እንዲደግፍና የማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጣቸውም አሳስበዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ባህልን በማሻሻል ታካሚዎች ወደ ህክምና ተቋማት ሲመጡ ከማጉላላት ይልቅ በትህትናና በርህራሄ ማስተናገድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የላፍቶ ሆስፒታል ካንሰርንና የልብ ሕመምን ጨምሮ ውስብስብ ሕክምናዎችን የሚሰጥ በመሆኑ፣ ንጽሕናውንና ውበቱን ጠብቆ ማስቀጠል የጤና ቢሮ የሁልጊዜ ኃላፊነት መሆን አለበት ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትምህርት ቤት ግንባታ፣ በምገባና በአስተማሪዎች ኑሮ ማሻሻል ያመጣውን ስኬት በጤናው ዘርፍም በመድገም ለሌሎች ክልሎች አርአያ መሆን እንዳለበትም አደራ ብለዋል።
ዘመናዊው የላፍቶ ሆስፒታል ዘመኑ የደረሰባቸው የሕክምና መሣሪያዎችን ያሟላ ሲሆን፣ የጤና ፍትሐዊነትንና ተደራሽነትን ከማረጋገጥ ባለፈ መዲናዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ውጥን ለማሳካት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግም ተመላክቷል፡፡
በአስማረ መኮንን