AMN- ኅዳር 4/2019 ዓ.ም
አንዳንድ የዓለም ሀገራት ያላቸውን ጸጋ እና የተለያዩ የልማት አቅሞቻቸውን በመጠቀም በኢኮኖሚ ከመልማት አልፈው ለትውልድ የሚተላለፍ አይበገሬ ሃብት ማፍራት ችለዋል፡፡
እነዚህ ሀገራት ዘላቂና አስተማማኝ ሃብት ከማካበት ተሻግረው የዓለም አጠቃላይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እስከ መምራት ደርሰዋል፡፡
ዓለም አራት የኢንዱስትሪ አብዮቶችን አልፋ አምስተኛውን ለመቀበል እየተሰናዳች ባለችበት በአሁኑ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሀገራት ግን ዛሬም ድረስ ያላቸውን ጸጋ ወደ ተደራጀ ሀገራዊ አቅም መቀየር ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ የቀደሙት መንግስታዊ ስርዓቶች ግብርና የኢኮኖሚ ምሶሶ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያውጁም እርሻውን ከበሬ ትከሻ ማውረድ ፣ ማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ዘርፍም ቢሆን በየዘመናቱ መልካም ጅማሮዎች ቢኖሩም እነዚህን ጥንስሶች ማሰባሰብ ፣ ወደ ተደራጀ አቅም መቀየር ፣ ማስቀጠልና አይበገሬ ኢኮኖሚን መገንባት አልተቻላቸውም፡፡
የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት እንደነበረች የሚነገርላት ኢትዮጵያ የነበራትን እምቅ ጸጋዎች ተጠቅማ ተከታታይና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚና ሃብት መፍጠር እና ወደ ቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ሲገባት አንጡራ ሃብቷን ሳትጠቀምበት ቀርታለች፡፡
ከዚህ በተቃራኒው የነበራት ስልጣኔ እያሽቆለቆለ ከመሄዱም በላይ ከተቀረው ዓለም በብዙ ርቀት ወደ ኋላ ለመቅረት ተገዳለች፡፡
ከዚህም አልፎ እጅግ በጣም በሚያስቆጭ ሁኔታ ድርቅ ፣ ረሃብ ፣ የውስጥ ግጭትና ጦርነት ፣ ኋላ ቀርነትና ድህነት መለያዋ እስከ መሆን ደርሷል፡፡
በአንደኛው የዓለም አካባቢ የሚፈጠር ቀውስና ጦርነት በዓለም አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ የገዘፈ ጫና በሚፈጥርበት በዚህ ዘመን ላይ ፣ ኢትዮጵያ ተጽእኖውን የምትቋቋምበትን አቅም መፍጠር አልቻለችም፡፡
በፖለቲካ ፣ በቴክኖሎጂና በዲጂታል ዘርፉም ቢሆን የተቀረው ዓለም ከፍተኛ አቅም የፈጠረ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ሐሳብና ፈጠራን የኢኮኖሚ ማዕከል ማድረግ ተስኗት ቆይታለች፡፡
በተለይ ቴክኖሎጂውና የዲጂታል ዘርፉ በተቀረው ዓለም ሰላምና ደህንነትን ከማስከበር አልፎ ጠንካራ ኢኮኖሚን እስከ መገንባት ቢደርስም በኢትዮጵያ ግን በሐሰተኛ ወሬ ሀገር ማፍረስ ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የሰለጠነው ዓለም ምድርን አልፎ ህዋን ወደ ማሰስ በተሸጋገረበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ግን ከኋላ ቀርነት ተላቅቃ ከዘመናዊው እውቀትና ዓለም ጋር ለመቀላቀል ግብግብ በመፍጠር ላይ ትገኛለች፡፡

ዓለም ከድንጋይ ዘመን እስከ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በብዙ የእድገት ለውጦች ውስጥ እያለፈ በሚገኝበት በዚህ ዘመን ላይ በአንድ ወቅት የስልጣኔ ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ለምን ወደኋላ ቀረች የሚለው ጥያቄ የበርካቶችን ምላሽ ይፈልጋል፡፡
ኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ ዓለም ላይ በኢኮኖሚና በስልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት የሀገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ እስከመጣል እንደሚደርስ የተገነዘበው የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የዘመናት ስብራት ለመጠገን እና ያላትን ጸጋዎች ወደ ተደራጀ ሀገራዊ አቅም ለመቀየር በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብርና ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ፣ በቱሪዝም ፣ በአገልግሎት ፣ በማዕድን ፣ በአገልግሎት ፣ በሎጀስቲክስ ፣ በጂዲታል ፣ በከተማ ልማት ፣ በኢኮኖሚ ሪፎርም እና በሌሎች ዘርፎች የተገኙት ውጤቶች የሀገሪቱን የብልጽግናና የስልጣኔ መዳረሻ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ፣ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የሚሰሩ ሥራዎች በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመሩ መሆናቸው ደግሞ ኢትዮጵያ በመፍጠር እና በመፍጠን መርህ ዘላቂና አቻዮ ኢኮኖሚ መገንባት እንደምትችል የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ታላቁን የኢትጵያ ህዳሴ ግድብ በራሷ አቅም በመገንባት ከራሷ አልፋ ቀጣናውን በኃይል በማስተሳሰር ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የብልጽግናዋ እና የስልጣኔዋ መሰረት የሆነውን የባህር በር ጥያቄ ለመመለስ ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚዋን ይበልጥ ከማሳለጡና ቀጣናዊ ሉዓላዊነቷን ከማስከበሩም በላይ ለቀጠይ የስልጣኔ ጎዞዋ ትልቅ መደላድልን የሚፈጥር ነው፡፡
ከውስጥና ከውጭ የሚቃጡባትን የደህንነት ስጋቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመመከት ታላቅ ሀገራዊ አቅም የፈጠረችው ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎቿን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ በአዲስ የሥራ ባህልና በቁጭት በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ