ኢትዮጵያ በኮፕ-31 የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ በብቃት የሚሳተፉ ወጣት ተደራዳሪዎችን እያፈራች ነው – የፕሬስ ሴክሬታሪያት

You are currently viewing ኢትዮጵያ በኮፕ-31 የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ላይ በብቃት የሚሳተፉ ወጣት ተደራዳሪዎችን እያፈራች ነው – የፕሬስ ሴክሬታሪያት

AMN – ኅዳር 4/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በኮፕ-31 (COP 31) የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ድርድር ላይ በብቃት እየተሳተፉ የሚገኙ ሙያዊ ብቃት ያላቸው ወጣት ተደራዳሪዎችን እያፈራች መሆኗን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ወ/ሮ ቢልለኔ ሥዩም ገለጹ።

ኃላፊዋ፤ አፍሪካ ኢትዮጵያን የኮፕ-32 (COP 32) አስተናጋጅ እንድትሆን የመረጠችው በሰጠችው ከፍተኛ እምነት መሆኑን ጠቁመው፣ ሀገሪቱ የራሷን ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱንም አጀንዳዎች ይዛ በድርድሮች ላይ በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች ብለዋል።

ለሚቀጥለው የኮፕ-32 ዓለም አቀፍ ጉባኤም ሁለገብ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ለጉባኤው በተዘጋጁት ዋና ዋና የሀገር ገጽታ ግንባታ ምሶሶዎች መሠረትም፤ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ለዓለም ኢኮኖሚ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ እያስተዋወቀች መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአትሌቶች መድረክ በሚለው ስያሜ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ አትሌቶች በተለያየ ወቅት የሚያስመዘገቡት ድልና ጽናት የሕዝቡ እውነተኛ መገለጫ መሆኑ በጉባዔዉ እየተዋወቀ ይገኛል።

ከዚህም ባሻገር ከ180 በላይ ሀገራት በተገኙበት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗ እየተዋወቀ መሆኑንም ጨምረዉ ገልጸዋል።

ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ከተሞችን ለመታደግ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተከናወኑ ሥራዎችም እንደ አንድ ዋና ትኩረት የተደረገበት መሆኑንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል ሀገሪቱ ያላት ምቹ የተፈጥሮ ጸጋና የ13 ወራት ፀጋ ለታዳሽ ኃይል ልማት ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በሶላር ኃይል ልማት ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ውጭ ገበያ ምርቶች እየቀረቡ ሲሆን፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተመረቁ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችም ለንጹህ ኃይል ሽግግር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሻራ ያረፈበት፣ ለንጹህ ኃይል ማመንጨት ያለውን የላቀ አቅም የሚያሳይ ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል።

የሃገር ገጽታን የሚገነቡ እነዚህ እና ሌሎች ሥራዎች በጉባዔዉ ለመላዉ እየተዋወቀ ይገኛል ብለዋል።

በመጪው ጉባኤ ወደ 80 ሺህ የሚጠጉ እንግዶችን ማስተናገድ መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ኃላፊነት ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እና የግል ሴክተሩ የጋራ ኃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የታወቁበትን እንግዳ ተቀባይነት በማሳየት፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በጥራት በማዘጋጀት እንግዶችን በብቃት ለማስተናገድ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review