ሐሳብ አልባ ያልተገራ ፖለቲካ እና መዘዙ!

You are currently viewing ሐሳብ አልባ ያልተገራ ፖለቲካ እና መዘዙ!

AMN – ኅዳር 5/2019 ዓ.ም

በሐሳብ የበላይነት የሚመራ ፖለቲካዊ ሥርዓት የአንድን ሀገር ዴሞክራሲያዊ ባህል ከማጠናከሩም በላይ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ የሐሳብ የበላይነትንና ውድድርን የማያበረታታ እንዲሁም የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠባብ ከሆነ፣ ለሕጎች መጣስና ለሰላም መደፍረስ ቀዳሚ መንስኤ ይሆናል።

ከሰለጠነ የውድድር ማዕቀፍ ውጪ የሆነ እና ያልተገራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ደግሞ ወደ ጽንፈኛ አስተሳሰብ የማምራት ዕድሉ ሰፊ ነው።

ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ማኅበረሰቡን ወደ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና የእርስ በርስ ጦርነቶች ይወስዳሉ።

አፍሪካን ጨምሮ አንዳንድ የአለም ሀገራት በዚሁ ጽንፈኛ እሳቤ ምክንያት እንደሚፈተኑ መረጃዎች ያመላክታሉ።

እነዚህ ሀገራት በሰላም እጦት የሚፈተኑት በሐሳብ የበላይነት የሚመራ ፖለቲካዊ ሥርዓት መገንባት ባለመቻላቸው ነው።

ጽንፈኛ ኃይሎች ከጠንካራ መንግሥት ይልቅ ሕገ-ወጥነትና ሥርዓት-አልበኝነት እንዲሰፍን ስለሚፈልጉ፣ የሐሳብ የበላይነት እንዳይጠናከር ያደርጋሉ።

በዚህም ሥልጣን ከሐሳብ የበላይነትና ከሕዝብ ይሁንታ ወጥቶ በጦር መሣሪያ አፈሙዝ እና በጉልበት እንዲወሰን በማድረግ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ይጥለዋል።

ያልተገራ ፖለቲካ በጋራ አብሮ የሚኖር ማኅበረሰብን እስከ መከፋፈልና ማጋጨት ይደርሳል።

ይህ እሳቤ አብዛኛውን ጊዜ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ ወይም በጎሳ ከፋፋይ ትርክቶች ላይ ይመረኮዛል።

በዚህ ጊዜ አሸናፊው ሐሳብና የሕዝብ ውሳኔ መሆኑ ቀርቶ ኃይልና ጉልበት ዋናው መለኪያ ይሆናል።

ሐሳብ-አልባ ፖለቲካ ዜጎች እንደ አንድ ሕዝብ ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ ከመተባበር ይልቅ፣ እርስ በእርሳቸው እንዲጠራጠሩና የጠላትነት ስሜት እንዲያዳብሩ በማድረግ ማኅበራዊ ትስስርን ያፈርሳል።

የሕዝቦች ሰላምና ደኅንነት የማያስጨንቃቸው እና ኃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም ሕዝቡን የሚከፋፍሉ ነጠላና ከፋፋይ ትርክቶችን ሆን ብለው ያሰራጫሉ።

ምክክር፣ መተሳሰብና መተዛዘን እንዳይኖር፤ ቂም፣ ቁርሾና በደል እንዲሰፋ በማድረግ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ መተማመንን ይንዳሉ።

በሐሳብ ድርቀት የሚፈጠር ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሥልታዊ በሆነ ሁኔታ የሀገርን ኢኮኖሚ እስከ መጉዳት ይደርሳል።

መንግሥት ለልማት፣ ለጤና፣ ለትምህርት እና ለሌሎች የሕዝብ አገልግሎቶች መዋል የነበረበትን በጀት ለጦርነትና ለጸጥታ ማስከበሪያ እንዲውል በማድረግ ኢኮኖሚውን ያባክነዋል።

በሐሳብ-አልባ ፖለቲካ ምክንያት የሚመጣ ውስጣዊ አለመረጋጋት የውጭ ጠላቶች ጣልቃ እንዲገቡ ምቹ መደላድልን ስለሚፈጥር የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ይጥላል።

እንደ ሻዕቢያ፣ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን፣ ሸኔ እና ፋኖ ያሉ ጽንፈኛ ኃይሎች በሰለጠነ ፖለቲካና በሐሳብ የበላይነት የማያምኑ፣ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚላላኩ፣ የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ሀገርን ለማፍረስ የሚቋሙጡ ናቸው።

ይህ እውነታ ተግባራቸው ሀገር አፍራሽ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ፣ ማንኛውም ፖለቲካዊ እሳቤ ሀገር የሚገነባበት መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ ሀገር አጥፊና የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ በሕግና በሥርዓት መቆጣጠርና መግራት ያስፈልጋል።

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ጠንካራ የፍትህ ተቋማትን መገንባት፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተገቢ ነው።

ከጽንፈኛና ከፋፋይ እሳቤ ወጥቶ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት መመቻቻልን እና ውይይትን ማጠናከር፣ እንዲሁም ሀገር በቀል ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን ማጎልበት ትልቅ መፍትሔ ነው።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review