
AMN- ኅዳር 11/2017 ዓ.ም
የመከላከያ ሰራዊቱን ጀግንነት የዘመኑ የውጊያ ሜዳ በሆነው “የሳይበር ምሕዳር” ላይም መድገም እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አማካኝነት ለሦስት ወራት ያህል የሳይበር ደህንነት የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲሰለጥኑ የቆዩ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ትዕግስት ሃሚድ የሳይበር ምህዳር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህል፣ የዲፕሎማሲ እና የወታደራዊ እውቀትና ፍልስፍናዎች የሚራመዱበት፣ የሚተሳሰሩበትና ለሁሉም ተዋናዮች እኩል እድልና አቅም ያስገኘ ምህዳር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህን በዉል የተገነዘቡ ሀገራት በመስኩ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋያቸዉን በማፍሰስና የሳይበር ጦራቸዉን መገንባት ችለዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት በደምና በአጥንቱ ያስከበረ ፍጹም ኢትዮጵያዊ እና ጀግና ሰራዊት መሆኑን እና ይህንኑ ሌሎች ሀገራትም ጭምር የሚመሰክሩለት መሆኑን ያመላከቱት ዋና ዳይሬክተሯ “ይህ የመከላከያ ሰራዊታችን ጀግንነት የዘመናችን የውጊያ ወይም የጦርነት ምህዳር በሆነው “የሳይበር ምሕዳር” ላይም መድገም ይገባል” ብለዋል፡፡
ለዚህም ምህዳሩን የሚመጥን እውቀት፣ ክህሎት እና አስተሳሰብ መላበስና በቀጣይነት እያሳደጉ መሄድ ግድ ይላል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የተወለደ ተቋም እንደመሆኑ መጠን የሰራዊቱን ሁለንተናዊ አቅም ለማጎልበት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ዋና ዳሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ መስኮች በጋራ ሲሰራ መቆየቱንና ወደፊትም በጋራና በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተመራቂዎቹ በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የብሄራዊ ደህንነት ስጋትን ለመቀነስ መሳሪያ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን ዘርፉ ተለዋዋጭና አዳጊ በመሆኑ ተመራቂዎቹ የሰራዊቱ አባላት ከዘርፉ ጋር አብሮ የሚሄድ ቀጣይነት ያለዉ የመማርና የማደግ ጉዟቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉበት ዋና ዳይሬክተሯ ማሳሰባቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡