
AMN – ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሎችና ከፍተኛ አመራሮች በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል ሌተናል ጀነራል አኬች ቶንግ አሉ ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር በሁሉን-ዓቀፍ የትብበር ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን የላከው መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ጠንካራ የሆነ ታሪካዊ፣ ባሕላዊና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላቸው ሀገራት እንደሆኑ በምክክር መድረኩ መነሳቱን ያመለከተው መረጃው፤ የጋራ ዕጣ-ፈንታቸውንና ሕልውናቸውን የሚወስኑ ዘርፈ-ብዙ ትብብሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁሟል።
የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ትስስር ለማረጋገጥ የሚገነባው የመንገድ መሠረት ልማት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑ በውይይቱ ወቅት መገለጹን ያመለከተው መረጃው፤ በዚህ ሂደት ከጸጥታና ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመረጃ ልውውጥና በጋራ በሚደረጉ ስምሪቶች መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን አስታውቋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በድንበር አካባቢ የሚታዩ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ የገንዘብና የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እንዲሁም የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የሚያደርጓቸውን የትብብር ሥራዎች አጠናክረው በመቀጠል ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈን ይሠራሉ።
ከዚህ ቀደም የደቡብ ሱዳን የመረጃና ደኅንነት አመራሮችና ባለሙያዎች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስልጠና መውሰዳቸውን ያስታወሰው መረጃው፤ በሰው ኃይል ዐቅም ግንባታ ረገድ የሚደረገው ትብብርም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጿል።
በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል የተመሩት የልዑካን ቡድኑ አባላት በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እና ሌሎችንም ፕሮጀክቶች የጎበኙ ሲሆን፤ በከተማዋ በሚታዩ ፈጣን ዕድገቶችና ለውጦች መደነቃቸውን እንደገለጹ መረጃው ጠቁሟል።
ሌተናል ጀነራል አኬች ቶንግ አሉ ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ሱዳን ኢንተርናል ሴኪዩሪቲ ቢሮ በዳይሬክተር ጀነራልነት በመሾም ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆናቸውን መረጃው የጠቆመ ሲሆን፤ በመረጃ፣ በደኅንነትና በጸጥታ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረጉት ትብብሮች ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድጉ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ መግለጻቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከው መረጃ አመልክቷል።