
AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያና የሶማሊያ የደኅንነት ተቋማት የአንካራው ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን ተፅዕኖ ለመከላከል ምክክር አደረጉ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የተቋሙ ስትራቴጂክ አመራሮች ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የሶማሊያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ኤንድ ሴኪዩሪቲ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አብዱላሂ ሞሐመድ ዓሊ ጋር በወቅታዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ አመልክቷል፡፡
የአንካራውን ስምምነት ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ከሁለቱ ሀገራት አቻ ተቋማት የሚጠበቁ የትብብርና የአጋርነት መስኮች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን መረጃው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያና ሶማሊያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሚፈጥሩ አካላትን ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት የጋራ መግባባት መድረሳቸውን፤ በተለይም በመረጃ ልውውጥና አቅጣጫም መቀመጡን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት የሚያደፈርሱ አጋጣሚዎች ተፈጥረው የነበረ ቢሆንም፤ የሁለቱ ሀገራት ዕድገት የተሳሰረ መሆኑ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀው አብሮነት ግንዛቤ ውስጥ እንደሚገባ በመድረኩ መነሳቱን የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ ገልጿል፡፡
አልሸባብ አሁንም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሥጋት ምንጭ መሆኑን የኢትዮጵያና የሶማሊያ የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በምክክር መድረኩ ማንሳታቸውን የጠቆመው መረጃው፤ የነበሩትን የዳበሩ ልምዶች በመቀመርና አዳዲስ የጸረ -ሽብር ትግል አጋርነትና ትብብር መስኮችን በማጠናከር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ተስማምተዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ የጋራ ስጋቶችን በትብብርና በምክክር በመፍታት ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማስፈንና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ተባብረው እንደሚሠሩ በምክክር መድረኩ መነሳቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃን ዋቢ አድርጎ ኢዜአ ዘግቧል፡፡