ጀግናዋ ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በረ/ ኮሚሽነርነት ማዕረግ ተሾመች

AMN ሰኔ 06/2018

‎ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በአራት የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ የ3 ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ እና የአንድ ጊዜ የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ትታወቃለች።

ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም አደባባይ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ካወለበለቡ ታላላቅ አትሌቶች መካከል ከ15 በላይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆና ስሟ በግባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

‎የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የስፖርት ክለብእና የሙዚቃና ቴአትር ቡድን 40ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል በአድዋ መታሰቢያ በዛሬው ዕለት ሰኔ 6 ቀን 2018 ዓ.ም የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ሀና አርዕያ ስላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና የስፖርትና የኪነጥበብ ቤተሰቦች በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት በተከበረበት ዕለት ነው የማዕረግ ሽልማቱ የተበረከተው።

በመርሃ ግብሩ ላይ ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ለረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ለኮማንደር ፋጡማ ሮባ፣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሽ ስህን፣ ለኮማንደር አትሌት ሰለሞን ባረጋ እና ለም/ኮ/ር ሰንበሬ ተፈሪ እንዲሁም ለሌሎች አንጋፋ ስፖርተኞች የዕውቅናና ሽልማት ፕሮግራም ተካሄዷል።

‎የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ለጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ጥሩነሽ ዲባባ የሰጠው ማዕረግ የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ ሲሆን ይህም የተቋሙ ከፍተኛ የማዕረግ ዕድገት ተብሎ የሚጠራ ነው።

በዕለቱ ‎በአትሌቲክሱ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሴትና ጥቁር አፍሪካዊት የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የ3 ኦሎምፒክ የወርቅ አሸናፊ የሆነችው ኮማንደር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ፣ የሶስት ጊዜ የአለም ሻምፒዮና በ10ሺ እና በ5ሺ የብር ሜዳልያ አሸናፊው ጀግናው አትሌት ስለሺ ስህንና የማራቶን ጀግናዋ ኮማንደር አትሌት ፋጡማ ሮባ ዕውቅና የተሰጣቸው ናቸው።

‎በአሠልጣኝነትም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ ከ 3 አስርት ዓመታት በላይ ያገለገለው፣ በ7 የኦሎምፒክ እና በ12 የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ታሪክ የማይረሳው ውለታ የዋለው፣ ከበርካታ ታላላቅና ውጤታማ አትሌቶች ጀርባ የሚገኘው አዳኙ አሰልጣኝ ረዳት ሚሽነር ሁሴን ሸቦ ኒሻን እንዲሸለም ሁኗል።

‎በተመሳሳይም የኮሚሽኑ የሙዚቃና ቴያትር ቡድን አባላት የነበሩት ድምፃዊ ደመረ ለገሰ ድምፃዊ ተፈራ ነጋሽ፣ ድምፃዊ ም/ኮ/ር መላኩ እንግዳ፣ አርቲስት ፍሬህይወት ስዩም፣ ሳክስፎኒስት ዘሪሁን በለጠ እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት መበርከቱን ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review