AMN-ሚያዝያ 9/2018 ዓ.ም
የአፍሪካ መዲና በሆነችዉ አዲስ አበባ ከቅርብ አመታት ወዲህ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን እድገትና ለውጥ የበርካቶች አጀንዳ እና መነጋገሪ ከመሆን አልፎ አህጉር እና ዓለም አቀፍ የተለያዩ ኩነቶችን ለማዘጋጅት ተመራጭ አድርጓታል፡፡
የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን ጨምሮ በመዲናዋ የተከናወኑ ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ህጻናትና ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከሉ መሆናቸው ደግሞ ፍትሃዊ ልማትን ከማስፈን ረገድ ያላቸው ድርሻ የጎላ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በቅርቡ በሰጡት ገለጻ፣ከለዉጡ ወዲህ በመዲናዋ ያከናወነው ልማት ብቻ ሳይሆን የልማት አብዮትም ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባን አዲስ ገጽታን ባለበሱ፤ የከተሜነትንና የዘመናዊነት አዲስ እሳቤ ባነገሱ የልማት ስራዎች አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ለአህጉርና አለም አቀፍ ጉባኤዎችና ሁነቶች ተመራጭ ከተማ ሆናች፡፡

አዲስ አበባ ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በሰራቻቸዉ የልማት ስራዎች የአፍሪካ እና የዓለም መሪዎችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች፤ ተጽእኖ ፈጣሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ደግመው ደጋግመው የሚጎበኟት መዲና እንድትሆን አድርገዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በስፖርትና መዝናኛ ስፍራዎች፤ በሕጻናት ክብካቤ፤ በኪነ ጥበብ ስራዎች፤ በትምህርትና ጤና፤ በአገልግሎት አሰጣጥ፤ በትራንስፓርት፤ በንግድና ኢንቨስትመንት እና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ያከናወናቸዉ የልማት አብዮቶች የመዲናዋን ተመራጭነት አጉልተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ለማስተናገድ መቻሏም ይህንኑ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን መንግስት ለስፓርቱ ዘርፍ ለሰጠዉ ትኩረት እውቅና የሚሰጥ ነዉ፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ነገ በሚካሄደው በዚህ ታላቅ ውድድር ከ70 በላይ ስመ-ጥር የዓለም አቀፍ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ አበባም እንግዶቿን ተቀብላ ውድድሩን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቃለች።

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ የውድድር ዳይሬክቴር ፒርስ ኦካላጋን “የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ” ለማዘጋጅት የተደረገውን ጥረት አድንቀዋል።
“ከስድስት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ትራክ አልነበረም ፤ አሁን ያየሁት ግን ተዓምር ነው፣ለመጀመሪያ ጊዜ በምታሰናዱት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ያሳያችሁት ጥረት አስደናቂ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለማዘጋጀት በምታስባቸው ውድድሮች ላይ ወርልድ አትሌቲክስ እገዛ እንደሚያደርግ ነዉ ፒርስ ኦካላጋን ያረጋገጡት፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ ሞሐመድ ውድድሩ በአዲስ አበባ መካሄዱ ለወደፊቱ ትላልቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት ሁነቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ