AMN — ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም
በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ከሚታዩ የጤና እክሎች መካከል አንዱ የሆነው የጨጓራ ባክቴሪያ፣ ተገቢው ክትትልና ሕክምና ካልተደረገለት ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ሊዳርግ እንደሚችል የሕክምና መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህ ባክቴሪያ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ የጨጓራን ውስጣዊ ግድግዳ ለአሲድ ተጋላጭ በማድረግ ሂደቱን ይጀምራል።
በሂደትም የጨጓራን ሽፋን በመሸርሸር ወደ ቁስለት፣ አልፎ ተርፎም ወደ ጨጓራ ካንሰር ሊያመራ እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍባቸው መንገዶች በርካታ ሲሆኑ፤ በተለይም በተበከለ ምግብና ውሃ፣ በምራቅ ንክኪ እንዲሁም የተበከሉ ቁሶችን በመጠቀም የሚከሰት ነው።
ሕመሙ በዋናነት ከንጽህና መጓደል ጋር ተያይዞ የሚከሰት በመሆኑ፣ በተለይ ሕፃናት ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።
የበሽታው ምልክቶች እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ሊለያዩ ቢችሉም፣ በዋናነት ግን ምግብ ከተበላ በኋላ በሆድ የላይኛው ክፍል ላይ የማቃጠልና የመደንዘዝ ስሜት፣ የሆድ መንፋት፣ ተደጋጋሚ ግሳት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና ያልታሰበ የክብደት መቀነስ ሊከሰቱ ይችላሉ።

በሽታው የጠነከረ ጥቃት ያደረሰባቸው ሰዎች ደም የተቀላቀለበት ትውከት ሊያጋጥማቸው እና የሰገራ ቀለም ወደ መጥቆር ሊቀየር እንደሚችልም ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
የምርመራ ሂደቱን በተመለከተም በትንፋሽ ውስጥ ያለውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን በመለካት፣ የሰገራ ናሙና በመውሰድ ወይም የኢንዶስኮፒ መሣሪያን በመጠቀም የባክቴሪያውን መኖር ማረጋገጥ ይቻላል።
ባክቴሪያው ያለባቸው ሰዎች በአንቲባዮቲክና አሲድን በሚቀንሱ መድኃኒቶች ሊታከሙ የሚችሉ ቢሆንም፣ እንደ አስፒሪንና ዲክሎፌናክ ያሉ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ያለ ባለሙያ ትዕዛዝ መጠቀም የጨጓራ ቁስለትን ስለሚያባብስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ይመከራል።
እጅን በሳሙናና በውሃ በመታጠብ እንዲሁም ንጹህ ውሃን በመጠቀም ከዚህ ባክቴሪያ መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ ከመገርጣት፣ ራስን ከመሳትና ከመተንፈስ መቸገር ጋር የተያያዙ ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች በአስቸኳይ ወደ ሕክምና ተቋም እንዲያመሩ ይመከራል።
በበረከት ጌታቸዉ