በመዲናዋ ጠንካራ አገልጋይ ተቋማትን የመገንባት ሽግግር…

You are currently viewing በመዲናዋ ጠንካራ አገልጋይ ተቋማትን የመገንባት ሽግግር…

AMN-ሚያዝያ 16/2018 ዓ.ም

አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደ ሃገር በተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የአገልግሎት መስጫ ማእከላት ክፍት ተደርገው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰራር የቢሮክራሲ እንግልትን፣ የጊዜ ብክነትን በማስቀረት በተበታተነ ቦታ ይሰጡ የነበሩ የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ መሶብ ነዋሪዎች ሳይጉላሉ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ይገኛል።

አዲስ መሶብ የተገልጋዮችን እንግልት በመቀነስ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እየረዳ ይገኛል፡፡

በዚህም በቦሌ፣ በልደታ፣ በአዲስ ከተማ፣ በጉለሌ እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ማእከላት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ዋል አደር ብሏል፡፡

ዲጂታል አሰራርን የሚያቀርበው አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ተገልጋዮች አገልግሎቱን አግኝተው እስኪመለሱ ድረስ ያለው ጊዜ በሙሉ በሲስተም የሚመዘገብና ክትትል የሚደረግበት መሆኑ ግልጽነት ያለው አሠራር ለማስፈን ይረዳል፡፡

አሰራሩ የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማሻሻል ባለፈ ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ለውጥ እያመጣ እንዲሁም ለሰው ተኮር አገልግሎት ለተሰጠው ትኩረትም የተግባር ማረጋገጫ እየሆነ ይገኛል፡፡

በመዲናዋ ቀደም ብሎ የነበረውን አሰራር ለማስፋት እንዲሁም ዜጎች ባሉበት አካባቢ እና በቤታቸው ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት አሰራርም በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ ሥራ የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ አገልግሎት ዜጎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም መሶብ የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ ዜጎች ሳይሆኑ አገልግሎቱ ወደ ዜጎች የሚመጣበትን ሐሳብ የያዘ ነው ፡፡

ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አግልግሎት የዜጎችን እንግልት የሚቀንስ እና ተጨማሪ ወጪን የሚያስቀር ሲሆን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደሆነም ይታመናል፡፡

የሀገር ዕድገት ለዜጎች በሚሰጥ አገልግሎት የሚወሰን ሲሆን የዜጎች ፈጣን አገልግሎት አለማግኘት ከእንግልት ባለፈ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና አለው፡፡

ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ አገልግሎት እየቀረበበት የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአዲስ አበባ ባሻገር ወደ ክልሎችም መስፋት ችሏል፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀናጀ አገልግሎት ለተገልጋዩ መስጠት የሚያስችል አሰራርም ሲሆን÷ የዲጂታል 2030 እውን ለማድረግ በኢትዮጵያ የታለመውን ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በሁሉም ክፍለ ከተሞች የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በቀሩት ክፍለ ከተሞች ም ማእከላትን ለማስፋፋት እቅድ መያዙን የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review