AMN – ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እያስመዘገበች የምትገኘውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስኬት በትምህርት ዘርፉ ላይም አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ ገለጹ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ በጀመረበት ወቅት ነው።
ዶ/ር ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳመለከቱት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየተደጋገሙ በሚፈጠሩበት በዚህ ወቅት የዲጂታል ቴክኖሎጂን አማራጮች መጠቀም ለትምህርት ዘርፉ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ እያስመዘገበችው ያለው ውጤት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ የትምህርት ዘርፉም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆንና በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ እንዲዘጋጅ የተደረገበት ዋነኛ ዓላማም በዘርፉ ላይ የተሰሩ ምርምሮችን በመመልከትና ውጤቶቹን ለትምህርት ጥራት መሻሻል ለማዋል መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።

በጉባኤው ላይ የታደሙት ከስዊድን ዩኒቨርሲቲ የመጡት ኤመሬተስ ፕሮፌሰር ቪናያጉም ሰርቬይ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂው ዘርፍ ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያደርገው ግስጋሴ ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የጀመረችው አርአያነት ያለው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መክረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ዓለም አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ምሁራን በአካልና በበይነ-መረብ አማካኝነት ተሳታፊ ሆነዋል።
በበላይሁን ፍስሃ