በአዲስ አበባ የሰላምና የጸጥታ ስራዎች አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ተገለጸ

You are currently viewing በአዲስ አበባ የሰላምና የጸጥታ ስራዎች አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ተገለጸ

AMN – ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በህብረተሰቡና በጸጥታ ኃይሉ ቅንጅታዊ አሰራር በአዲስ አበባ ከተማ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ ማስፈን መቻሉን የከተማዋ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አካሂደዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቷ እየጨመረ መጥቷል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ በህብረተሰቡና በጸጥታ መዋቅሩ የተቀናጀ ጥረት የተገኘው አስተማማኝ ሰላም ቁልፍ ሚና ማበርከቱን አስረድተዋል።

በተለይም በበጀት ዓመቱ ውስጥ በርካታ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኩነቶች ያለምንም የጸጥታ ስጋት በስኬት መጠናቀቃቸው የከተማዋን ሰላም ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመዋል። ከጸጥታ ስራው ጎን ለጎንም የከተማዋን የደንብ ጥሰቶችን ለመከላከል ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በጸጥታ መዋቅሩና በነዋሪው መካከል ያለው ትብብር መጠናከሩ ለደንብ ማስከበር ስራው ውጤታማነት መሰረት መሆኑን አብራርተዋል።

ቢሮ ኃላፊዋ በቀጣይ ትኩረት ስለሚደረግባቸው ጉዳዮች ሲያብራሩም፤ መጪው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ኃይሉ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የጸጥታ መዋቅሩም የተጀመሩ ስኬታማ ስራዎችን በቁርጠኝነት በማስቀጠል ለከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲተጋ አሳስበዋል።

በአለሙ ኢላላ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review