AMN – ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ያለማው የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂ ተመርቋል፡፡
የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ስርዓት ቴክኖሎጂ የተሰኘው አዲሱ ሲስተም የተደራጀ መረጃን በመያዝ ተጠያቂነትን በማስፈን በመረጃ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም በሚል መርህ በሁሉም ተቋማት ስራን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎች እያበለፀገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የለማው የመገናኛ ብዙኃን የሀገር ገፅታን በመገንባት እና ተፅእኖ በማሳደር ያለውን ጉልህ አቅም በመረዳት የሚሰሩ ሥራዎች እንዲዘምኑ እና ተጨባጭ መረጃን ለመመዝገብ እንዲቻል ብሎም ሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ተግባር ለማገዝ መሆኑን አንስተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ በሁለቱ ተቋማት የለማው ቴክኖሎጂ ባለስልጣኑ በአዋጅ ያገኘውን የመገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር እና ክትትል ስራ በዘመናዊ መልኩ ለመስራት የሚያግዝ እና የሚሰራጩ ይዘቶች ምንነትን ለማወቅ እና የሀሰት መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ለመገናኛ ቡዙኃን ደረጃ ለመስጠት፣ የዜጎችን ጥቆማ ለመቀበል እና በመረጃ የተደገፈ እርምጃ ለመውሰድ ብሎም ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያግዝም አመላክተዋል፡፡
የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ቴክኖሎጂ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በቤተልሔም አየነው