AMN- ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ በቤት ግንባታ ዘርፍ መሰማራት የሚያስችለውን ታሪካዊ ስምምነት ተፈራመ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በመሪዎች ደረጃ የጋራ የልማት ትብብር በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት መደረሱን ተከትሎ በኮርፖሬሽኑ እና በደቡብ ሱዳን ማዕከላዊ ኢኳቶሪያል ግዛት መካከከል በቤት ልማት ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈጽሟል፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና በደቡብ ሱዳን የማዕከላዊ ኢኳቶሪያል ግዛት መንግሥት መካከል የተደረገው ይህ የመግባቢያ ሰነድ፣ በጁባ ከተማ በቤቶች ልማትና አስተዳደር ዘርፎች በጋራ መሥራት የሚያስችል መሠረት መጣሉን ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) እና የማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛት መንግሥት አስተዳዳሪ ኢማኑኤል አዲል በይፋ መፈረማቸውን ኢዜአ በዘገባው ጠቅሷል።

ይህ ውል ኮርፖሬሽኑ ያለውን የረጅም ጊዜ ልምድና የቴክኒክ አቅም በመጠቀም በጁባ ከተማ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ሕንፃዎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲያከናውን ሰፊ መንገድ እንደሚከፍትም ተመላክቷል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ረሻድ ከማል በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ ባስቀመጠው ራዕይ መሠረት በምሥራቅ አፍሪካና በመላው አህጉሪቱ ገበያዎች ለመሰማራት ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ አሁን ላይ ወደ ተግባር ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ኮርፖሬሽኑ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውና አዋጭ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።